በአንጋፋው ጋዜጠኛ አበራ ለማ አተያይ የራዲዮ ተፅዕኖ አሳዳሪነት እንዳለ ሆኖ፤ ከአንድ ራዲዮ ጣቢያ ብቻ ስርጭት በነበረባት አገረ ኢትዮጵያ የኢትዮጵያ ራዲዮ ተፅዕኖ በእጅጉ ብርቱ እንደነበር ያስታውሳል።
እንደ "ብርቄ" በባትሪ የሚሠሩ ራዲዮኖች ገጠር ደርሰው፤ የኢትዮጵያ ራዲዮ ስርጭቶችን ለሕዝብ በማዳረስ ረገድ አስተዋፅዖ ማድረጋቸውንም ይጠቅሳል።
ሬዲዮ ሕዝብ ላይ ትልቅ አስተዋፅዖ አሳዳሪ መሳሪያ ነውጋዜጠኛና ደራሲ አበራ ለማ
አበራ ለማ፤ ጋዜጦች ከራዲዮ ጋር በንፅፅሮሽ ሲታዩም ወደ ገጠሩ ሕዝብ በዝተው አይደርሱ እንደነበር ያነሳል።
ሆኖም ለከተሜውና ለተማረው ወገን ጋዜጦችም ብርቱ ሚና ነበራቸው ሲል ይጠቅሳል።
የወቅቱን የኤሌክትሮኒክና የሕትመት ብዙኅን መገናኛ ሲያነሳ ግና በእጅጉ የሚያሳስቡት፤ ለሕፍረትም የሚዳርጉት ጉዳዮች አሉ።
ጥራትና ሥነ ምግባር
አበራ፤ በአንጋፋ የጋዜጠኛነት መነፅሩ የተመለከታቸው የሕትመት ውጤት የሆኑት ጋዜጦችና መጽሔቶች ጥራት ደረጃ በእጅጉ ዝቅ ያለ ሆኖ ታይቶታል።
ለወቅቱ የብዙኅን መገናኛ ስርጭቶች የጥራት ደረጃ መውረድ በሙያው ላይ የተሠማሩቱ ጋዜጠኞች "የዕለት ደራሽ" ሥራ ላይ መጠመድ አንዱ ጉልህ አስባብ እንደሁ ያመላክታል።
አክሎም "በሬ ወለደ" ዓይነት የተጋነኑ ርዕሶችን የያዙ የሕትመት ውጤቶች በሐሰተኛ መረጃ ስርጭት መከሰስ፣ የሕትመት ዋጋዎች አለቅጥ መናር ለጋዜጦችና መጽሔቶች ክስመት አስተዋፅዖ ማድረጋቸውንም ይጠቅሳል።
በተያያዥነትም፤ በራዲዮ፣ ቴሌቪዥንና ጋዜጣ ላይ በጋዜጠኛነት ሙያ የተሠማሩ ግለሰቦች በቂ ስልጠና አለማግኘት፣ በሙያው የመብሰልና የሰከነ ዝግጅት ያለማድረግ በብዙዎቹ እንደሚታይና እንደሚንፀባረቅም ይናገራል።
ጋዜጠኞቹ ከድርጅታቸው የውሎ አበል ተቀብለው ከሙያው ሥነ ምግባር ውጪ ዳግም የጋበዟቸውን ድርጅቶች የውሎ አበል ክፈሉን፤ የገንዘብ ጉርሻም ስጡን ማለትን በጣሙን እሳዛኝ የሥነ ምግባር ግድፈት አድርጎ በሙያ አክባሪነትና ተቆርቋሪነት መንፈስ ያነሳል።
ጋዜጠኛ በድለላና በጉቦ አይሠራምጋዜጠኛና ደራሲ አበራ ለማ
ተጨማሪ ዋቤ ሲጠቅስም፤ በርካታ ጋዜጠኞች ኩነቶች ላይ እንዲገኙ ተጋብዘው የሚመጡት ከአንድ እጅ ጣቶች የማያልፉ እንደሆነና "ለምን?" ሲባልም "እነሱ'ኮ በእጅ ካላሏቸው አይመጡም" የሚሉ አሳፋሪ ምላሾች እንደሚሰሙ ይጠቅሳል።
"አንገት አስደፊ" በማለትም በሙያዊ ቁጭት ገልጦታል።
ጊዜው በሙያም፣ በሥነ ምግባርም ለማካን መሰልጠንን ግድ እንደሚል በማመላከት "ለወደፊት ፕሬሱ ወደ የት እንደሚሔድ አላውቅም" ይላል።
ይህን የታዘበው ከቋሚ መኖሪያው ኖርዌይ ወደ አገር ቤት ብቅ-መለስ በሚልባቸው አጋጣሚዎች ነው።
ከአገር ቤት ወደ ባሕር ማዶ
አበራ ለማ፤ የግሉ ፕሬስን ብርቱ ፈተና መግጠምና የቀድሞ የኢሕዲሪ ጋዜጠኞች በኢሕዴግ የሻጉራ መታየት ታክሎበት አገር ለመልቀቅ ግድ ተሰኘ።
ለጥገኝነት ጥየቃ ኬንያ ዘለቀ።
ስደተኛ ሆነ። በስደት ሕይወት ተፈተነ።
ጥቂት ቆይቶም በለስ ቀናው። የአገረ ኖርዌይ ዳግም ሠፋሪ ሆነ።
የኖርዌይ የሠፈራ ሕይወቱ ከኬንያው የስደት ሕይወቱ ቢሻልም፤ አዲስ ቋንቋ መማር፣ የአየር ንብረትን መላመድ፣ ሥራ ፈልጎ ማግኘትና ከቤተሰብ ጋር ዳግም አዲስ ኑሮን በአዲስ አገር መጀመሩ ሌላ የሕይወት ተግዳሮቶች ሆኑ።
እንዲያም ሆኖ፤ እራሱን ከአዲሱ የመኖሪያ አገሩ ጋር አላመደ። አዋደደ።
ከጋዜጠኛነቱ፤ የድርሰት ሕይወቱ ሚዛን ደፋ።
ተጨማሪ ያድምጡ
አበራ ለማ፤ ከመምህርነት ወደ ጋዜጠኛነትና ደራሲነት