አበራ ለማ፤ ከመምህርነት ወደ ጋዜጠኛነትና ደራሲነት

A Lemma Pic.png

Journalist and Author Aberra Lemma. Credit: A.Lemma

ከኢትዮጵያ አንጋፋና ስመ ገነን ጋዜጠኞችና ደራሲዎች ውስጥ ቀዳሚ ተጠቃሽ ከሆኑቱ ውስጥ አበራ ለማ አንዱ ነው። በማስታወቂያ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ራዲዮና አዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ በግሉ ፕሬስ በአዕምሮ ጋዜጣ የጋዜጠኛነት ድርሻውን አበርክቷል። በድርሰት በረከቶቹም ሰሞነኛውን "የዓለማችን ምስጢራት" መፅሐፉን አክሎ ከ20 በላይ መፅሐፍትን ለተደራሲያን እነሆኝ ብሏል።


ትውልድና ዕድገት

የአበራ ለማ ትውልድ ቀዬ ደገም ወረዳ ሰላሌ ነው።

ወላጆቹ የኦሮምኛና አማርኛ ቋንቋዎች ተናጋሪ ስለነበሩ የአፍ መፍቻ ቋንቋዎቹ አማርኛና ኦሮምኛ ናቸው።

በአንደበቱ እንደገለጠው "ጥሩ እረኛ" ባይሆንም ከእረኞች ጋር ውሏል። ውርንጭላ ጋልቧል። እንኩቶ አንኩቷል።

ደስተኛ የልጅነት ጊዜን አሳልፏል።

ፊደልም ቆጥሯል።

ከቄስ ትምህርት ቤት ወደ መምህርነት

አበራ በቄስ ትምህርት ቤት ፊደል የቆጠረውና "አስኳላ" ገብቶም የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ያጠናቀቀው ፍቼ ነው።
Aberra Lemma 5A.jpg
Student Aberra Lemma in Fiche. Credit: A.Lemma
በቀዬው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስላልነበረ በምደባ ወሊሶ ደረሰው።

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እዚያው አጠናቀቀ።

ለቀጣይ ዕውቀት ሸመታ ኮተቤ የመምህራን ማሰልጠኛ ገባ።

ከአንድ ዓመት ስልጠና በኋላ በመምህርነት ተመረቀ።

በድልደላ የጎንደር ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አስተማሪ ሆነ።

ነጭ ጠመኔውን ጥቁር ሰሌዳ ላይ እየቀለመ ማስተማር ጀመረ።

ዕውቀትን የአገሩ ተስፈኛ ወጣቶች አዕምሮ ውስጥ ዘራ።

የቀለም አባት ሆኖ ለሁለት ዓመታት ቆየ።

በ1968 ዓ/ም ጎንደርን ለቅቆ አዲስ አበባ ዘለቀ።

ወሊሶ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተጠነሰሰው የሥነ ፅሑፍ ፍቅሩ ገንፍሎ ወጣ።

መምህርነትን አሌ አለ።

ከመምህርነት ወደ ጋዜጠኛነት

እምባዛም ሳይቆይ የማስታወቂያ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ራዲዮንና የአዲስ ዘመን ጋዜጣን ሁነኛ መድረኮች እነሆኝ አለው።

"ትምህርት ሰውን ሙሉዕ ያደርጋል" በሚለው አመኔታው ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዘልቆ የዲፕሎማና ዲግሪ ባለቤት ሆነ።

የቀለም ቃለ ነቢብና ግብርን ማዋደድ ያዘ።

በጋዜጠኛነቱ ላይ ድርሰትን አከለ - ጋዜጠኛና ደራሲ አበራ ለማ።
በጋዜጠኛነት ሙያ ፍቅሬን ገልጬበታለሁ፤ ኖሬበታለሁ።
አበራ ለማ
ያኔ እንደ ዘንድሮ ዘመናዊ የሚዲያ ቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን ምጡቅ ባይሆኑም፤ ወቅቱ ያፈራቸውን የምስልና ድምፅ መቅረጫዎችን ግና ተገልግሎባቸዋል።
Aberra old machine.jpg
Journalist Aberra Lemma. Credit: A.Lemma
ከምሥራቅ እስከ ሰሜን ጦር ግንባር ይዟቸው ዘምቷል - በጦር ሜዳ ጋዜጠኛነት።

በሰሜን ጦር ግንባር የጦር ሜዳ ሙዋዕለ ዜናዎችን ይዘግብ የነበረው ከ501ኛ ግብረ ኃይል ሠራዊት ጋር ተካትቶ ነበር።

ከጦር ሜዳ በፊልምና በድምፅ አቀናብሮ የመዘገቡ ሂደት ያልተለመደ በመሆኑ "ድንቅ" ተሰኘ።
Abera war front.jpg
Journalist Aberra Lemma at the war front. Credit: A.Lemma
"የጦር ሜዳው ቀሲስ" የሚል ቅፅል ስምም አተረፈ።

ከጦር ሜዳ መልስ ግና የኢትዮጵያ ራዲዮ የውስጥ ፖለቲካዊ ሽኩቻዎች አይለው ቆዩት።
ጋዜጠኛነት አልጋ - በአልጋ አይደለም። ድፎ ዳቦ ተሆኖ ነው የሚሠራው፤ ከላይ እሳት፤ ከስር እሳት።
ጋዜጠኛና ደራሲ አበራ ለማ
ጎራ የከፈላቸው የብሔራዊ አንድነት አራማጆችና በተቃርኖ የቆሙቱ ፍልሚያ የከረረ ሆነ።

ጋዜጠኛ አበራ ለማ የኢትዮጵያ ራዲዮን ተሰናበተ።

የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢሕዲሪ) መንግሥት በኢሕአዴግ የሽግግር መንግሥት ተተካ።

የነፃ ፕሬስ አዋጁን ተከትሎም የአዕምሮ ጋዜጣ ላይ ከአዳዲስ ወጣት ጋዜጠኞች ጋር ሠራ።

የግሉ ፕሬስ ላይ ፈተናዎች በዙ።

የአበራ ዕጣ ፈንታ ስደት ሆነ።
Lemma Norway.png
Aberra Lemma. Credit: A.Lemma

Share