የአንድ ትውልድ ዕድሜ የሕትመት ጉዞ
የሩብ ክፍለ ዘመን ጉዞው አሳታሚውን ኤልያስ ወንድሙንና የፀሐይ ሕትመት ድርጅትን ክሽፈት ለብርቱ ፈተናዎች የዳረጋቸውን ያህል፤ ስኬት ሐሴትና ሞገስን አላብሷቸዋል።
ኤልያስ ከትውልድ አገሩ ኢትዮጵያ ተነጥሎ አገረ አሜሪካ መኖሪያው ከመሆኗ በፊት ወጣት ጋዜጠኛ ነበር።
ከአገሩ ቢልየም ከሙያው ግና አልተየም።
በአገረ አሜሪካም በመጽሔትና ሬዲዮ ጋዜጠኛነት ቀጠለ።
ወደ አሳታሚ ድርጅት አገልግሎት ያመራው ከእናቱ ወ/ሮ ፀሐይ ሕልፈተ ሕይወት በኋላ ነው።
የአሳታሚ ድርጅቱ መጠሪያ "ፀሐይ" መሰኘት ለወላጅ እናቱ ዝክረ መታሰቢያነት ባሻገር፣ በሕይወትና ሕልፈት የእናት ልጅ የማይዳሰስ ሕያው የማይበጠስ ውጪያዊና ውስጣዊ መቆራኛነት ዕሳቤም ጭምር ነው።
ፀሐይ የሕይወት ምንጭ እንደሆነች ሁሉ፤ ዕውቀትም የሕይወት ምሰሶ ናትና የኢትዮጵያውያን፣ አፍሪካውያንና ምዕራባውያን ማለፊያ የአዕምሮ ጭማቂ የሆኑቱን ትሩፋቶች በሕትመት ውጤቶቹ ለአያሌዎች ለማዳረስ በቅቷል።
ከዋነኛ ሕልሞቹ አንዱ የኢትዮጵያን ያልተነገሩ ታሪኮችን ለሕትመት አብቅቶ ለትውልድ የሚበጁ ዘመን ተሻጋሪ ቅርሶችን ሰንቆ ማድረስ ነውና ባለፉት 25 ዓመታት እንዲያ ሲከውን ሩብ ክፍለ ዘመን አጎምርቷል።
ተግዳሮችና ስኬቶች
የፀሐይ አሳታሚ ድርጅት ምሥረታ የወረቀት መጽሐፍት በኤሌክትሮኒክስ መጽሐፍ የቴክኖሎጂ ጉልብትና ተጎሽመው በርካታ የኢትዮጵያን ታሪክ ሲያሳትም የነበረው የሐዋርድ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ ከአራት አሠርት ዓመታት የሕትመት አገልግሎት የተገፋበት፤ የእንግሊዙ ሃይማን አሳታሚ ድርጅትም የአፍሪካ ሥነ ጽሑፍ ቅርንጫፉን የዘጋበት ወቅት ነበር።
ይሁንና የኤልያስ የሕይወት ጥሪና የአዕምሮ ፈተና ግና ኪሣራና ትርፍ አልነበረም። ዕውቀትን ያማከለ ታሪክ ለሕትመት አብቅቶ ለትውልድ ይድረስ ማለት እንጂ።
መልካም ርዕይ በበጎ ዕሳቤ ብቻ ዕውን አይሆንምና ማሳተሚያ ገንዘብና ድርጅቱን በክህሎት ለስኬት የሚያበቁ ባለሙያዎችን ማግኘት ቀዳሚ ተግዳሮቶቹ ሆኑ።
ጓደኞቹ 'ይቅርብህ' ሲሉ መከሩ።
አዕምሮውን እንደሳተም ቆጠሩ።
ኤልያስ፤ ከቶውንም የብድር ካርዶችን ተጠቀመ።
የጡረታ አበል ተቀማጩን አውጥቶ ለፀሐይ ሸረፈ።
ዝቅተኛ ሥራዎችን ሠርቶ ለሕትመት አዋለ።
የተወሰኑ መጽሐፎችን ለማሳተም በቃ።
የተልዕኮው ግዝፈት የፈተናዎቹን ክብደት አቅልሎ እንዲያይ ውስጣዊ ኃይል ሆኑት።
ዛሬ ላይ ቆሞም አዋኪዎቹን ጊዜያት በምልሰታዊ ምልከታ እየተመለከተም ያ ጊዜ ተመልሶ ቢመጣ ትናንት የከወናቸውን ዳግም እንደሚተገብር ሳያመነታ ይናገራል።
የ25 ዓመታት ጉዞዎቹ ግና በፈተና ወጀቦች ብቻ ሳይሆን በስኬት ሞገስ አላባሽነትም የተመሉ ነበሩ።
ከአያሌ ስመ ጥር ሰዎች ጋር አውለውታል፣ ዕውቀት ገብይቶባቸዋል፣ ለአደባባይ ከበሬታና በርካታ ሽልማቶችም አብቅተውታል።
በቅርቡም፤ ከ15 ዓመታት በላይ በዩኒቨርሲቲ ያገለገለባትና ለ20 ዓመታት የኖረባት የሎስ አንጀለስ ከተማ ምክር ቤት በምክር ቤቱ ስም ባለቤቱ ድምፃዊት ቤቲ ጂ፣ ልጁ ሉላ፣ አባቱና የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ አባላት በተገኙበት ዕውቅናን ቸሮታል።
ኤልያስ የምክር ቤቱን ሽልማት ፋይዳ አስመልክቶ "የኢትዮጵያን ታላቅነት፣ የታሪካችንን ዓለም አቀፍ ይዘት ያለው መሆንና ካከበርነው እኛም እንደምንከበር ነው ያየሁበት" ብሏል።
Elias Wondimu, Founder and Publisher of the Tsehai Publishers and Distributors contributions in literature, culture and inclusivity, received the prestige award of the Los Angeles City Council award with his wife, Singer Betty G, on September 15 in Los Angeles City Council. Credit: E.Wondimu
የሕይውት አካል ምስክርነት
የኤሊያስ ባለቤት ድምፃዊት ቤቲ ጂ ግና " ኤሊያስ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን፣ ለመላው ጥቁር ዘርና ለዓለም ለለፋው ልፋትና ላሳየው ትጋት ይኼኛው ክብር ሲያንሰው ነው ብዬ መግለፅ እችላለሁ" ባይ ናት።
"ስለምን ሌትና ቀን የሚያሳስበውና የሚያስጨንቀው ነገር ቢኖር፤ የኢትዮጵያ ነገር፣ የአፍሪካ በአጠቃላይ የጥቁር ሕዝብ ትልቅ ቦታ ደርሶ ለማየት የሚመኝ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ነው ያገኘሁት። ሁልጊዜም በጣም የሚያስደስተኝና የምኮራበት ጎኑ ነው"
"እኔም አገሬንና ሙዚቃን ብወድም ከኤልያስ ጋር በመሆኔ ለአገሬ ያለኝ ዕይታና ፍቅር የበለጠ እንዲጨምርና እንድወደው አድርጎኛል። ሽልማቱ እኔም የምሠራቸውን ሥራዎች ከእዚህ የሚወርዱ ሳይሆን፤ ከእዚህ ከፍ ያሉ እንዲሆኑ ያደርገኛል"
"ገና ወደፊት ከእዚህ አልፈን ብዙ እንሠራለን፤ ለብዙዎች እንደርሳለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ" ብላለች ።
ኤሊያስና ቤቲ ጂ በቀጣዩ ክፍል የቤቲ የ Loyola Marymount ዩኒቨርሲቲ ተጋባዥ የሙዚቃ መምህርትነት ለግሏና ለኢትዮጵያ ስላላቸው ፋይዳዎችና የወቅቱን የኢትዮጵያ ሁኔታ አስመልክተው በጋራ ስላስተላለፉት መልዕክት ይናገራሉ።
ተጨማሪ ያድምጡ
ድምፃዊት ቤቲ ጂ ከመድረክ ወደ ዩኒቨርሲቲ የሙዚቃ መንበር