"የስዕል ሥራዎቼ የሚያንፀባርቁት የመጣሁበትን የኢትዮጵያ ማኅበረሰብና በግሌ ያለፍኩባቸውን የሕይወት ጉዞዎቼን ነው" - አርቲስት አላና ዳመና ጃንፋ

Olana GAWF.png

Artist Olana Janfa and his "Get A White Friend" paint. Credit: SBS Amharic / OD.Janfa

አርቲስት ኦላና ዳመና ጃንፋ፤ ውልደትና ዕድገቱ አዲስ አበባ ቄራ ሠፈር ነው። ገና የ16 ዓመት ዕድሜ ሳለ የአገር ውስጥ ሁኔታ አመቺ ባለመሆኑ ሳቢያ ከታናሽ ወንድሙ ጋር ለአገረ ኖርዌይ ነዋሪነት በቃ። እህል ውኃው ግና ከኖርዌይ ይልቅ አውስትራሊያ ሆነ።


አንኳሮች
  • ውልደትና ዕድገት
  • የኑሮ ጅማሮ በአገረ ኖርዌይ
  • ፍቅር፣ ቤተሰብና ሥነ ስዕል በአውስትራሊያ
የኑሮ ጅማሮ በአገረ ኖርዌይ

ኖርዌይ ከአየሯ ቀዝቃዛማነትና አያሌ ኢትዮጵያውያንን አቅፋ ካለመያዟ በስተቀር ለኦላናና ታናሽ ወንድሙ በሕዝቧ መልካም መስተንግዶ፣ የቋንቋና ትምህርት ዕድል ችሮታዋ አላስከፋችውም።

ከኖርዌይ ወደ አውስትራሊያ

ሕይወት በአንድ ቀዬ፣ አገር፣ ሥራና ትምህርት ብቻ የተገታች አይደለችምና ኦላና የሶስት ሳምንታት የዕረፍት ጊዜውን አውስትራሊያን በመጎብኘት ለማሳለፍ ወሰኖ ተነሳ።

የአውስትራሊያ መድብለ ባሕልና የጥበብ ሥራዎች መዲና ወደሆነችው ሜልበርን ከተማ በክረምት ወር ገባ።

በበረዷማይቱ ኖርዌይ ንፅፅር አየሩን ወደደው። "ድንቅ" ሲል አሞካሸው።

ይህን ሲል የሰሙ አውስትራሊያውያን "ይህ'ኮ የክረምት አየር ነው። በበጋ ብትመጣ ምን ልትል ነው?" ሲሉ በአግራሞት ጠየቁት።

እንዲያ ከሆነማ በማለት ወደ ኖርዌይ ተመልሶ የአንድ ዓመት መቆያ ቪዛ ይዞ ዳግም ወደ አውስትራሊያ ተመለሰ።

ክረምቱ በበጋ በተተካበት ወቅት "ፀሐዩ የኢትዮጵያ የልጅነት ዕድገቴን አስታወሰኝ" አለ።

በምናባዊ ምልሰት የአገር ቤት ትዝታዎቹ ግዘፍ ነስተው፤ የሰመመን ሕይወት ተላብሰው ፊቱ ተደቀኑ።

ሜልበርን የትውልድ አገሩን በሚያስናፍቅ ሰውነትን በለብታ በሚዳስስ የፀሐይ ሙቀትና ብርሃኗ ልጋሴ ብቻ አላበቃችም። ከቶውንም፤ ከልጆቿ አንዲቷን ወጣት ሴት እነሆኝ ብላ ለሕይወት ተጋሪነት ቸረችው።

የመልካሚቱ ሴት ፍቅር ልቡን ገዛው። እምብዛም ሳይቆዩ ከፍቅረኝነት ለባልና ሚስትነት በቁ። ሲልም የመጀመሪያ ልጃቸውን አፈሩ።
Olana and his Family.jpg
Olana and his family. Credit: OD.Janfa
ዓለም አቀፍ ዝንቅ ጋብቻዎች ቁጥር በዘመነ ሉላዊነት እየጨመረ ባለበት ሁነት የኦላናና አውስትራሊያዊት ባለቤቱ ቅይጥ ጋብቻ በፍቅር የታጀበ ታካይ የሕይወት ጉዞ ሆነው።

በቅይጥ ጋብቻ ውስጥ በዝምታ የሚገለጥ የስሜት ተግባቦት አንዱ የልብ ለልብ መደማመጫ መለያ ነው። በኦላና ሕይወት ውስጥም የራሱ ሚና አለው።

"ባለቤቴ ከቋንቋ የበለጠ ስሜቴን አይታ ትረዳለች። ይህም ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ባሕልን ታውቃለች፤ ታከብራለች። አገሯን አውስትራሊያንም ትወዳለች" ሲል የተግባቦት ደረጃቸውን ገልጧል።

ስለ መልካም ሰውነቷም አንስቶ "ጥሩ ሕይወት ነው ያለኝ። በጣም ጥሩ ሰው ናት። ጥሩ ሕይወት ነው የሰጠችኝ" በማለት ሞገስ አላብሶ አንስቷታል።

ከተመልካችነት ወደ ባለ ብሩሽነት

ኦላና እንደ አያሌ ኢትዮጵያውያን የስዕል ሥራዎችን ተመልክቶ "ቆንጆ" እና "መጥፎ" ብሎ ከማለፍ የዘለለ እምብዛም የገፋ የሥነ ስዕል ግንዛቤ አልነበረውም።

ይሁንና በአንዲት የምሽት አጋጣሚ የሕይወት አቅጣጫው የሥነ ጥበብ ፈለግን መከተል ጀመረች።

ኦላናና ባለቤቱ አንድ ሆቴል ታድመው ሳለ ዓይኖቹ አንድ የቅብ ሥራ ላይ አረፉ። ስዕሉ ቀልቡን ገዛው። አጋጣሚ ሆኖም ሰዓሊው እዚያው ነበርና ተነጋገሩ።

ኦላና ጥንታዊ የኢትዮጵያ ሥነ ስዕሎችን አፍቃሪና አድናቂ ነበርና "ይህን ስዕል ለምን አትስልልኝም?" ሲል አንድ ጥንታዊ አገርኛ የሥዕል ሥራን ለሰዓሊው አሳየ።

ሰዓሊው እያቅማማ "ምናልባት እሞክረው ይሆናል" ሲል ምላሽ ሰጠው።

የሁለቱን ውይይት ያደመጠችው ባለቤቱ "ለምን አንተ እራስህ አትሠራውም?" ስትል ጥያቄና አስተያየቷን አቀረበች። የማበረታቻ ሃሳቧንም አጠናክራ ድጋፏን እንደምትቸረው ገለጠች።

በማግሥቱ ስዕል እንደምን እንደሚሳል ራሱን በራሱ ማስተማር ጀመረ። ጥቂት ቆይቶም የሠራቸውን የስዕል ውጤቶቹን ለወንድሙና ለጓደኞቹ መላክ ቀጠለ።

የወንድሙና የጓደኞቹ ምላሾች አድናቆቶችን የተላበሱ ነበሩ።

አድናቆታቸውን "እውነት ነው" ብሎ በማመን ራሱን እያስተማረ በስዕል ሥራው ገፋ።

እምብዛም ሳይቆይ ከአንዲት አውስትራሊያዊት የሥነ ጥበብ ጋዜጠኛ ጋር ተዋወቀ። ሥራዎቹን ተመልክታ አድናቆቷን ቸረችው። አልፋም፤ ስዕሎቹን ወስዳ ለሌሎች ባለሙያዎች አሳየችለት።

"ማለፊያ ሥራ" ተባለለት።

የራሱን የስዕል ፍላጎት ለማርካት ብሩሽና ቀለሙን ያዋደደው ኦላና ስዕሎቹ ከመኖሪያ ቤት ወደ አደባባይ ለሕዝብ ዕይታ መብቃት ያዙ።
Money.jpg
Credit: Olana Janfa.
ቀደም ሲል በቡድን ያቀረባቸውን ሁለት የስዕል ኤግዚቪሽኖችን ተከትሎ፤ በ2021 ራሱን ችሎ አንድ የስዕል ኤግዚቪሽን ለሕዝብ ዕይታ አበቃ።

የኦላና የጥበብ ሥራዎቹ ለሕዝብ ዓይነ ገብ የሚሆኑባቸው መንገዶች ዘርፈ ብዙ ናቸው።

የጎዳና ላይ ስዕሎች፣ የፋሽን ትዕይንቶች፣ ምስል የተላበሱ ካናቴራዎችና የትላልቅ ኩባንያ መለያዎች ከቅብ ሥራዎቹ በተጨማሪ ጎልተው የሚታዩ ናቸው።
Olana Tshirt.jpg
Credit: Olana Janfa.
ኦላና ለሁለተኛ ጊዜ በግሉ የሚያቀርባቸው ሥራዎቹ ዘንድሮ በ2023 እስከ ኦገስት 24 በቪክቶሪያ ኢሚግሬሽን ሙዚየም ለሕዝብ ዕይታ ቀርበዋል።






Share