ጃኑዋሪ 26 ለአውስትራሊያውያን ነባር ዜጎች ምን ማለት ነው?

BRISBANE INVASION DAY RALLY

Invasion Day Rally, Brisbane 2024. Source: AAP / JONO SEARLE

ጃኑዋሪ 26 በሀገረ አውስትራሊያ ብሔራዊ ቀን ነው፣ አከራካሪነቱ ግና ቀጥሎ አለ። ለአውስትራሊያ አዲስ የሆኑ አያሌ ፍልሰተኞች የአዲሲቷን ሀገራቸውን ክብረ በዓል ማክበር ይሻሉ፤ ሆኖም ከቀኑ ጀርባ ያለውን ሙሉ ታሪክ መረዳት በጣሙን አስፈላጊ ነው።


Key Points
  • የአውስትራሊያ ቀን በ1788 በሲድኒ ኮቭ የእንግሊዝ ዩኒየን ጃክ የተውለበለበበት ቀን ሲሆን፤ ቅኝ ግዛት የተጀመረበት ዕለተ መነሻም ነው።
  • ጃኑዋሪ 26 የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት መጀመሪያ፤ ለአቦርጂናልና ቶረስ መሽመጥ ደሴት ቀሳፊ የታሪክ አካል ነው።
  • በሕዝብ አስተያየት ስብስቦች መሠረት አብዛኛዎቹ አውስትራሊያውያን የአውስትራሊያ ቀን ጃኑዋሪ 26 ላይ ፀንቶ እንዲቆይ ይሻሉ።
ጃኑዋሪ 26 ይፋዊ የአውስትራሊያ ቀን ነው፣ የሀገሪቱ ብሔራዊ ቀን።
ግና ለነባር ዜጎችና ቁጥራቸው እየጨመረ ላሉ አውስትራሊያውያን ይህ ቀን ከበሬታ የሚቸረው ቀን አይደለም።

ቦኢ ስፒሪም፤ የጋሚላራይ፣ ኮማ፣ የሙራዋሪ አንቂናና ፖድካስተር ዕለቱ የሚያሳድረውን ስሜታዊ ክብደት ሲገልጡ፤

“ለእኔ፣ ዕለቱ ላይ ስደርስ፣ ጠዋት ላይ የሚሰማኝ ስሜት ወደ ቀብር የምሄድ ያህል ነው። አንድ ክፉ ሁነት እንደተከሰተ አውቃለሁ። በጣሙን ሁከት የተመላበት ስሜት ያሳድራል። ” ብለዋል።

የአውስትራሊያ ቀን ጃኑዋሪ 26 የሚከበረው ስለምን ነው?

ጃኑዋሪ 26, 1788 የእንግሊዝ ሰንደቅ ዓላማ ሲድኒ ኮቭ ላይ የተውለበለበበትና የቅኝ ግዛት ጅማሮም ዕለት ነው።

የአውስትራሊያ ቀን ከ1935 ጃኑዋሪ 26 አንስቶ ታስቦ ቢውልም፤ ብሔራዊ ሕዝባዊ ክብረ በዓል ቀን መሆን የጀመረው ግና በ1944 ነው።

የተወሰኑ አውስትራሊያውያን ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን ዕለቱን የብረት ምጣድ ጥብስ በመጥበስ፣ ወደ ባሕር ዳርቻ በመሔድ ወይም ርችቶችን በመመልከት ያከብሩታል። በዕለቱ አያሌ የዜግነት ቅበላ ሥነ ሥርዓቶችም ይካሔዳሉ።

ይሁንና ከ1938 አንስቶ ጃኑዋሪ 26 በአቦርጂናልና ቶረስ መሽመጥ ደሴተኞች ዘንድ "የሐዘን ቀን" በሚል ተቃውሞ ደርሶበት አለ። ቁጥራቸው እየበረከተ ያለ አውስትራሊያውያንም ቀኑን ለማክበር እምቢኝ እያሉ ሲሆን፤ የብሔራዊው ክብረ በዓል ቀንም ወደ ሌላ ቀን እንዲዛወር እየጠየቁ ይገኛሉ።
BRISBANE INVASION DAY RALLY
Invasion Day Rally in Brisbane, 2024 Source: AAP / JONO SEARLE

ቀኑ ለአውስትራሊያውያን ነባር ዜጎች አሳማሚ የሆነው ስለምን ነው?

ዶ/ር ሰመር ሜይ ፊናሊ፤ የዮርታ ዮርታ ሴትና በዉሎንጎግ ዩኒቨርሲቲ ገዲብ መምህርት፤ ጃኑዋሪ 26 ከመነሻው ለአቦርጂናልና ቶረስ መሽመጥ ደሴት ሰዎች ተምሳሌነቱ ሰቆቃ ነው ሲሉ ያስረዳሉ።

“የዘረኛነት መነሻ ነው፣ የመድልዖ መነሻ ነው፣ ለሰዎቻችን ቀደምት አባቶቻችንና እናቶቻችን ለ65 ሺህ ዓመታት ከተጓዙበት የቀዬአቸው ማኅበረሰብ የተነጠሉበት ወቅትም ነው” ሲሉ።

የእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ፤ የመሬት ነጠቃ፣ ጅምላ ጭፍጨፋ፣ ለበሽታ መዳረግና ልጆቻቸውን በኃይል ለተነጠቁ ነባር ዜጎች በእጅጉ ጎጂ ነበር።

ተቋማዊ መድልዖ፣ ለጉስቁልና የተዳረገ የጤና ውጤቶች፣ በእሥር ቤት ከፍተኛውን ቁጥር መያዝን ያካተተው የቅኝ አገዛዝ ተፅዕኖዎች ዛሬም ድረስ ጫናቸው ሰርፆ አለ።

ዶ/ር ፊናሊ አውስትራሊያውያን የሀገራቸውን ታሪክ እንዲማሩ ያበረታታሉ።

“በአያሌ ዘርፎች አውስትራሊያ ድንቅ ሀገር ናት ብዬ አስባለሁ። እርግጠኛ ነኝ፤ ወደ እዚህች ሀገር መጥተው አሁን ዜጎች ሆነው ያሉቱ ይህንን ይገነዘባሉ። ይሁንና በተመሳሳይ መልኩ እዚህች ሀገር ውስጥ መልካም ያልሆነና በተለይም ዕውቅናም ያልተቸረው ታሪክ አለን” ይላሉ።

ቀኑን መቀየር፣ ዕውቅና መቸር ወይስ መክላት?

የሕዝብ አስተያየት እንደሚያመላክተው ከሆነ ይሁንና በየዓመቱ፤ የብሔራዊ ቀኑ እንዲለወጥ የሚፈልጉ ሰዎች እየበረከቱ ነው።

በርካታ አውስትራሊያውያን ነባር ዜጎች ቀኑ ከእነአካቴው እንዲከላ ሲሹ፤ የተወሰኑቱ ለታሪክ ዕውቅናን መስጠት ቅድሚያ እንዲኖረው ይፈልጋሉ። ሌሎች ቦ ስፒሪምን የመሳሰሉቱ፤ ቀኑ ከእነአካቴው መከላት አለበት የሚል አመኔታ አላቸው።

አያይዘውም “ይህ ይህች ሀገር የቀናችው በሰላማዊ መንገድ ነው ወይም ለነባር ዜጎች ዕውቅናን መቸር ሲገባ ያለመሆኑን የቅኝ አገዛዝ አረዳድ መክላት ነው። የነጭ የበላይነት ፅንፈኞችንና ዘረኞችን፤ እንዲሁም ለዋነኛው ሕዝብ ዘር ማጥፋትን ከእንግዲህ ወዲያ ማክበር አትችሉም፤ ትክክል አይደለም የሚል ማሳሰቢያም ነው” ብለዋል።
MELBOURNE INVASION DAY RALLY
People gather outside Victorian Parliament for the Invasion Day rally, 2024. Source: AAP / Diego Fedele

ጃኑዋሪ 26ን እንደምን ክብር በተመላው ሁኔታ ማክበር እንደሚገባ

የነባር ዜጎች ቡድን ጃኑዋሪ 26ን "የወረራ ቀን" ወይም "የሕልውና ቀን" ብለው በመጥራት ጉዞዎችን፣ የተቃውሞ ሠልፎችን፣ የንጋት አገልግሎቶችንና ባሕላዊ ኩነቶችን በመላው ሀገሪቱ ያካሂዳሉ።

ዶ/ር ፊንላይ እለቱ እንደምን እንደሚከወንና እንማን ተሳታፊም እንደሚሆኑ ሲገልጡ፤

“በተቃውሞ መግለጫነት ጎዳናዎች ላይ የሚካሔዱት ሠልፎች ሰላማዊ ሠልፎች ናቸው። ሜልበን እኖር በነበረበት ወቅት በሁለት ሠልፎች ተሳትፌያለሁ። የቦርጂናልና ቶረስ መሽመጥ ደሴት ቤተሰቦችም ይሁን ላልሆኑቱ አብሮ ለመሰባሰብ በጣሙን ድንቅ መንገድ ነው” ብለዋል።

ራና ሐሰን፣ ነባር ዜጎች በሆኑትና ባልሆኑት መካከል ዕርቅን የሚያስተዋውቀውና አትራፊ ያልሆነው ዕርቅ አውስትራሊያ ፋውንዴሽን የቦርድ አባል ናቸው። ስብስቦቹ ተስፋና አንድነት እንደሚያበረክቱ ሲናገሩ፤

“የአጋርነት መንፈስን ያገኛሉ፣ እናም ያን ዓይነት ስሜትም ማኅበረሰቡ ውስጥ ያገኛሉ። እንደ አጋርነታችን፤ ይህ ቀን ለእነሱ ምን ማለት እንደሆነ፣ ቀኑን ለመለወጥ ወይም ተጨማሪ ዕውቅናን ለመግኘት እየገፉ ባሉበት ወቅት ከነባር ዜጎች ጀርባ መቆሙ ስለ እውነት ጠቃሚ ነው” ይላሉ።

በርካታ ማዘጋጃ ቤቶች የጃኑዋሪ 26 ኩነቶችንና የዜግነት ቅበላ ሥነ ሥርዓቶችን ማካሔድን አቁመዋል። የተወሰኑ መሥሪያ ቤቶችም ሠራተኞቻቸው ዕለተ ዕረፍታቸውን ከሕዝባዊ ቀኑ ይልቅ በሌላ ቀን እንዲጠቀሙበት ፈቅደዋል።
New Australian citizens
New Australian citizens, Broken Hill, NSW Source: AAP / STUART WALMSLEY

ስደተኞች ከአውስትራሊያውያን ነባር ዜጎች ጋር እንደምን ይጎዳኛሉ

አቶ ስፒሪም፤ ጦርነትና ቅኝ ግዛትን ያዩ አብዛኛዎቹ ፍልሰተኞች የነባር ዜጎችን ትግሎች ይረዳሉ።

“ሰዎች እዚህ መጥተው አንዳች ዓይነት ሰላም ማግኘት አስደማሚ ነው። እኛ ከጃኑዋሪ 26 ቀን 1788 አንስተን ፍትሕን አላገኘንም፣ ሰላምንም አላገኘነም” በማለት ገልጠዋል።

ራና ሐሰን በበኩላቸው የጃኑዋሪ 26 ጉዳይ የነባር ዜጎች ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሁሉም አውስትራሊያውያን ጉዳይ ሊሆን እንደሚገባ ሲያስቡ፤

“እንደማስበው በርካታ ሰዎች ይህ ውስብስብ፣ ሐዘንና ሁከት የነባር ዜጎች ባቻ እንደሁ አድርገው ያስባሉ፤ ይሁንና የእዚያን ቀን ክብደት ለሚረዳ ማንኛውም ሰው ውስብስብነቱ ይሰማዋል። ለእኔ፤ እንደ አንድ የሕንድ ፍልሰተኞች ልጅነቴ፤ የራሳችን ቅኝ ግዛትና የእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ታሪክ አለን” ብለዋል።
ወ/ሮ ሐሰን፤ እንደ ሁለተኛ ትውልድ ፍልሰተኛ፤ ፍልሰተኞች እንደምን አዲሱን ማንነታቸውን ሊያክብሩ እንደሚሹ እረዳለሁ ባይ ሲሆኑ፤

ይሁንና ሁሉም አውስትራሊያውያን ሁሉን አቀፍ ብልሃትን አፈላልገን እስከምናገኝ ድረስ፤ ስለ እውነተኛ የሀገሪቱ ታሪክ ብርቱ የሆነ የሐሳብ ልውውጥ ሊያደርጉ እንደሚገባ ያምናሉ።

“እንደ ሀገር የሃሳብ ልውውጥ ልናካሔድ ይገባናል፤ ከእዚያ ቀጥለን ሁላንችንም በጋራ ልናከብረው የምንሻውና ዕውቅናንም የምንቸረው ታሪክ ላይ ተሰባስበን በመወያየት የትኛውን ቀን ለማክበር እንደምንወድ መነጋገር እንችላለን ብዬ አስባለሁ” ብለዋል።
ስለ አዲሱ የአውስትራሊያ ሕይወትዎ ተጨማሪ ጠቃሚ መረጃና ፍንጮች ለማግኘት የአውስትራሊያ ስትገለጥ ፖድካስትን ይከተሉ አሊያም ደንበኛ ይሁኑ።   

ጥያቄዎች ወይም ርዕሰ ሃሳቦች ካለዎት? በ ኢሜይል ይላኩልን።

Share