ደራሲ ታክሎ ተሾመ፤ ውልደታቸው ደሃና ገብርኤል ቀበሌ - ጎርጎራ ነው።
ፊደል ያስቆጠሯቸው የአብርጃ አርባ ተንሳ ቤተክርስቲያን መሪጌታ ብርሃን መንፈሳዊ ናቸው።
የቆሎ ተማሪ ነበሩ።
የቆሎ ተማሪ ለአዕምሮው የዕውቀት ማዕድን ከመምህሩ፤ ለአካሉ ጥሬም ሆነ ቁራሽ እንጀራ የሚያገኘው አኮፋዳውን ይዞ "ስለ ምንተማሪያም" ብሎ ከቀዬው በመለመን ነው።
የራራ ይቸረዋል፤ የሌለው ማርያም እንድትቸረው ይመኝለታል።
በቆሎ ተማሪ ሕይወት ውስጥ እንደ አቋቋም፣ ዝማሬና ቅኔ ዘረፋው ሁሉ የመንደር ውሻ አንዱ የግለ ታሪክ ትውስታ ነው።
የያኔው የቆሎ ተማሪ አዳነ በኋላ ታክሎ ተሾመ ከውሻ ጋር ቁራሽ ተናጥቀዋል፤ በሽመል መክተዋል።
ይሁንና ሁሌም በለስ አይቀናምና አንድ ቀን ሽመላቸው መክቶ አልዳናቸውም፤ እግሬ አውጪኝ ብለው ሮጠው አላመለጡም።
በአንድ የሠፈር ኃይለኛ ውሻ እግራቸውን ተነከሱ።
ደማቸውን እየዘሩ፤ ዕንባቸውን እያፈሰሱ መሪጌታ ዘንድ ደረሱ።
መሪጌታ ግና ከርህራሄ ይልቅ በአርጩሜ ሸነቆጧቸው።
ታክሎ መሪጌታ ላይ አዘኑ።
የፊደልና መንፈሳዊ ትምህርታቸውን አሌ ብለው አስኳላ ገቡ።
የጎርጎራ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ሆኑ።
ዓመታት ተቆጥረው ክፍሎች ተደምረው ለሁለተኛ ደረጃ ተማሪነት በቁ።
Grade 8 National Exam photo of Taklo Teshome. Credit: T.Teshome.
የመጨረሻው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መስከረም 2 ቀን 1967 ከዙፋናቸው ወረዱ።
የዘውዱ ሥርዓት በጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ተተካ።
Emperor Haile Selassie of Ethiopia (1892-1975) at a parade in Ethiopia in 1972 (L), and Mengistu Haile Mariam (1978-), an Ethiopian politician who was the most prominent officer of the Derg, the Communist military junta that governed Ethiopia, and the President of the People's Democratic Republic of Ethiopia (1987 - 1991) (R). Credit: Rolls Press/Popperfoto via Getty Images/Getty Images / Universal History Archive/Universal Images Group via Getty Images
የመላ አገሪቱ ተማሪዎች ሳይማር ያስተማራቸውን ሕዝብ እንዲያስተምሩ የመሠረተ ትምህርት ዘመቻ አወጀ።
የ11ኛ ክፍል ተማሪው ታክሎ ተሾመም የፊደል ሠራዊቱን ተቀላቀሉ።
የመራዊ ዘመቻ ጣቢያ የዕድገት በኅብረት የመሠረተ ትምህርት ዘማች ሆኑ።
መሠረተ ትምህርትና ፖለቲካ
መራዊ ዘመቻ ጣቢያ ውስጥም ፊደል አስቆጠሩ፣ ለአካባቢው ገበሬዎች የመፀዳጃ ቤቶችን ሠሩ፣ የመሬት ለአራሹን አዋጅ ተከትለው መሬት አደላደሉ።
The Ethiopian National Literacy Campaign (1979). Credit: T.Teshome
የማርክሲዝም ሌኒንዝም ርዕዮተ ዓለም አራማጅ ሆኑ።
ደርግና ኢሕአፓ ሁለቱም የማርክሲዝም ሌኒንዝም ርዕዮተ ዓለም አራማጆች ቢሆኑም በአተያያቸው ይለያዩ ነበርና ልዩነታቸው ተካርሮ ለጠብ ተዳረሱ።
ሲልም፤ ነፍጥ ተማዘዙ።
በትጥቅ የበላይነት የነበረው ደርግ ኢሕአፓን ከፖለቲካም ከትጥቅ ትግሉም ሜዳ ማስወጣት ቻለ።
ኢሕአፓ ህቡዕ ገባ።
ስደት አንዱ የኢሕአፓ አባላት ሕይወት ማዳኛ አማራጭ ሆነ።
ታክሎም ከራርመው ወደ አውስትራሊያ መሻገሪያ ወደ ሆነቻቸው አገረ ሱዳን አቀኑ።