ሶስና ወጋየሁ፤ ከሜክሲኮ አደባባይ እስከ ሀገረ አውስትራሊያ

Sosina Wogayehu I.png

Sosina Wogayehu. Credit: S.Wogayehu

ሶስና ወጋየሁ፤ ስርከስ ኢትዮጵያ ካፈራቸው ምርጥ ኮከቦች አንዷ ናቸው። ከሜክሲኮ አደባባይ ውልደትና ዕድገታቸው እስከ አውስትራሊያ የጥገኝነት ጥየቃ ሕይወታቸው ያወጋሉ።


ውልደትና ዕድገት

የሶስና ውልደት ሜከሲኮ አደባባይ ከሚገኘው የቀድሞው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካ (አሁን ኢትዮጵያ) ቅጥር ግቢ ነው።

የአንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሽመልስ ሃብቴ ተከታትለዋል።

የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት ሕይወታቸው በአያሌ ውጣ ውረዶች ተሸብባ በነበረችባት ሀገረ አውስትራሊያ ነው።

የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከስዊንበርን ዩኒቨርሲቲ፤ ሁለተኛውን ከብሔራዊ ሰርከስ ትምህርት ቤት ተቀብለዋል።

ወደ ጂምናስቲክ ዓለም የገቡት ገና የስድስት ዓመት ልጅ ሳሉ ሲሆን፤ ያኔ ሰርከስ ኢትዮጵያ ገና አልተመሠረተም።

እሳቸውም ቢሆን ቤታቸው ሳሎን ውስጥ ከመገለባበጥና በሰባት ዓመታቸው ወ.ወ.ክ.ማ / ወሴክማ ሔደው ጂምናስቲክ ከመሥራት ባለፈ ሰርክርስ ጥበብ መሆኑን አያውቁም ነበር።

ጥረታቸው ፍሬ ማፍራት ጀመረ።

የዘጠኝና 11 ዓመት ልጅ ሳሉ በጂምናስቲክ ውድድር ሻምፒዮን ለመሆን በቁ።

ክህሎትና ሽልማቶቻቸው ዓይን ውስጥ አስገቧቸው።

ሰርከስ ኢትዮጵያ የጥበብ ሕልውና ተላብሶ ሶስናን ከወወክማ ወሰደ።

እምብዛም ሳይቆዩ ከ25 የሰርከስ ቡድኑ አባላት ጋር ሆነው ወደ ሀገረ ኔዘርላንስ አቀኑ።

ንግሥቲቱ ፊት የመጀመሪያ ትዕይንቶቻቸውን አሳዩ።

ከታዳሚዎቹ መካከልም የአውሮፓ ሰርከርስ ሥራ አስኪያጆች ነበሩና በከህሎቶቻቸው ተደነቁ።

አንድናቆቶቻቸውን ብቻም ገልጠው አልተገቱ፤ ሰርክርስ ኢትዮጵያ በአውሮፓ የተለያዩ ከተሞች ተዘዋውሮ ትዕይንቶቹን አንዲያሳይ ጋበዙ።

እነ ሶስናም ብርቅዬ የሰርከስ መድረክ ከዋክብት ሆኑ።

አውሮፓ መነሻቸው እንጂ መድረሻቸው አልሆነም።

ይልቁንም ወደ ሀገረ አውስትራሊያ አቀኑ።

ሰርከስ ኢትዮጵያ በአደላይድ፣ ሲድኒና ካንብራ ትዕይንቶች ላይ ድንቅ የተባሉለትን ትዕይንቶቹን ለተመልካቾቹ አደረሰ።

ግና፤ ሶስናን አካትቶ በለጋ የወጣትነት ዕድሜያቸው 15 የሰርከስ ኢትዮጵያ አባላት አውስትራሊያን ጥገኝነት ጠየቁ።

የሜልበርን ነዋሪ ኢትዮጵያውያንም እጆቻቸውን ዘርግተው፤ በሮቻቸውንና ልቦቻቸውን ከፍተው ተቀበሏቸው።

ወ/ሮ ሶስና እስካሁንም ድረስ በተለይም የአቶ ጋሻው አንለይና የባለቤታቸውን ወ/ሮ መርዲያን መስተንግዶ ለዘላለሙ በማይረሳ ውለታነት ያነሳሉ።

እንዲያም ሆኖ፤ የሰርከስ ኢትዮጵያ ኮከቦች የአውስትራሊያ ሕይወት ጉዞ ጅማሮ ቀልብን በሚገዛ የጽጌረዳ አበባ መናፈሻ መካከል የመራመድ ያህል ቀልብን ማራኪና መዓዛውም ተምጎ መንፈስን አዳሽ አልነበረም።

ከቶውንም የሚያደርጉትንና የሚጠብቃቸውን የሕይወት ጉዞ ለማያውቁቱ ለጋ ወጣቶች አስጨናቂና አስለቃሽ ሆነ።

ወደ ሃገር ቤት ላለመመለስ ከወሰኑቱ ለጋ ወጣቶች ውስጥ የ11 ዓመት ልጅ ይገኝበታል።

ቀናት፣ በሳምንታት ሲልም በወራት ተትክተው መንፈቅ ሞላቸው።

ሶስና በስድስት ወራት ጊዜያት ውስጥ ከፀጉር ሥራ እስከ የሴቶች ሰርከስ ስልጠና ደረሱ።

መደበኛ ትምህርትም ጀመሩ።

የወ/ሮ ሶስና ወጋየሁ ግለ ታሪክ ትረካ በእዚሁ አላበቃም፤ በቀጣዩ ክፍለ ዝግጅትቻን እንደምን ለትልቁ የአውስትራሊያ ሰርከስ ሕይወት እንደበቁና ስለምን ወደ ሃገር ቤት ለመመለስ እንደሻቱ ያወጋሉ።







Share

Recommended for you