ውልደትና ዕድገት
የዕፀገነት አሰፋ የውልደት ሥፍራ የኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባ ናት።
የአምስት ዓመት ልጅ ሳሉ አባታቸው ከእዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።
የአባታቸው ማረፍ የመምህርት እናታቸው መኖሪያ የሆነችው የመንዝና ግሼ አውራጃ - መሀል ሜዳ ከተማ የለጋ ሕይወታቸው መቀረጫና መጎልመሻቸው ሆነች።
ብሩህ ተማሪ ነበሩና የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምርታቸውንም በየክፍሉ አንደኛ በመውጣት እዚያው አጠናቀቁ።
የላቀ የትምህርትና ሙያዊ የሥራ ዕድል ተስፋ ሰንቀው ወደ ሀገረ አሜሪካ አቀኑ።
የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳሉ የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪ ነበሩና አሜሪካ እንደደረሱ የፋርማሲ ትምህርት መስክን መረጡ።
የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ቀጠሉ።
በአዲስ አገር አዲስ ሕይወት
ወደ አዲስ አገር ሲሔዱ ስኬትን ማለም ቀዳሚ ዕሳቤ ቢሆንም፤ ዕውነታው ግና አዲስ ሕይወትን ከአልቦ ጀማሪ ለሆነ ቀርቶ ለሀገሬውም ቢሆን ኑሮ በብርቱ ትግል የሚታለፍበት አዘቦታዊ ሂደት ነው።
ፍልሰተኞች በተስፋ ጭላንጭልና በትናንት ሕልም ውስጥ የኑሮ ትግልን ለማሸነፍ ግድ የሚሰኙባቸው አያሌ አስባቦች አሉ።
ቋንቋ፣ ባሕል፣ ባይተዋርነትና ናፍቆትን መቋቋምና ከአስተዳደራዊ ሥርዓት ጋር እራሳቸውን ማሳለጥ፤ ፍልሰተኞች በወራት ወይም በዓመታት ጊዜያት ውስጥ የሚወጧቸው አንኳር ተጠቃሽ አይቀሬ የሠፋሪ ፈተናዎች ናቸው።
ዕፀገነት አሰፋም በእዚያ ውስጥ ማለፋቸው እውነት ነው።
እያንዳንዱ የዕለት ተዕለት እርምጃ ተግዳሮት አለው። በመቆየት ከስህተቴም እየተማርኩ መልመድ፤ ማወቅ ችያለሁ። ከሁሉ በላይ የእኔ ተግዳሮት የነበረው፤ ከቤተሰብ ብቻ ሳይሆን፤ ከሀገር በመለየቴ ምክንያት ከማንነት ጋር በተያያዘ ጠለቅ ያለ ጎዶሎነት ተሰምቶኝ ነበር።ዶ/ር ዕፀገነት አሰፋ፤ በፍሬድ ማየር - ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ የፋርማሲ ባለሙያ
ከዕፀገነት ቀድመው የአሜሪካ ነዋሪ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ፈጥኖ ደራሽ ሆነው አገር አላማጅ፤ ወገን አዛማጅ ሆኗቸው።
የመሸጋገሪያ ድልድይ ዘረጉላቸው።
ዕፀገነትም እንደ መሀል ሜዳ ንቁ ተማሪነታቸው ፈጥነው ከማኅበረሰባቸው ጋር ተቀላቀሉ።
አልፈውም፤ ከሀገሬው ጋር ተዛነቁ።
ቀዳሚ ትልምና ግባቸውን ሳይስቱ ትኩረታቸውን ትምህርታቸው ላይ አሳረፉ።
ሙያዊ ክህሎት መቅሰም ያዙ፤ በሕይወት ተሞክሮዎች ጎመሩ።
ዛሬ፤ የትናንት ተሞክሮዎቻቸውን ተመርኩዘው ለአዲስ የባሕር ማዶ ሠፋሪ ፍልሰተኞች ምክረ ሃሳባቸውን ያጋራሉ።
የሠፈራ ሂደታቸውን ቢያቃልል በሚል ቸር ዕሳቤ።
[ፍልሰተኞች] በቅድሚያ ምን ሊያደርጉ እንደሚሔዱና ስለሚሔዱበት ሀገር ሁኔታ የተወሰነ ግንዛቤ ሊኖራቸው ይገባል።ዶ/ር ዕፀገነት አሰፋ፤ በፍሬድ ማየር - ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ የፋርማሲ ባለሙያ
በፆታ ረገድም ሴትነት ሁለተኛ ተግዳሮት እንደሚሆን ልብ ያሰኛሉ።
ሆኖም፤ በቂ ግንዛቤና ዝግጀት ካለ ተሰናካክሎ መቅረትና ትልቅ መደናቀፍ ላይገጥም እንደሚችልም ያመላክታሉ።
በግላቸው ግና ሀገር ቤት ሳሉ መምህርት እናታቸው እራሳቸውን በሰብዕናቸው እንጂ፤ በተለይ በፆታቸው ፈርጀው እንዳያዩ መክረውና አበረታተው ስላሳደጓቸው የፆታ ፈተናዎችን እንደ ትልቅ ተግዳሮት አይመለከቱም።
አዲስ ፍልሰተኛ ኢትዮጵያውያን ሴቶች የፆታ ብቻ ሳይሆን የቆዳ ቀለም ተግዳሮቶችም እንደሚገጥማቸው ያሳስባሉ።
ትምህርት ቁልፍ የከፍታ መወጣጫ መሰላል እንደሆነ በመጠቆምም ርቆ የመጓዣ መንገድን ይጠቁማሉ።
ፍልሰትና ትምህርት
ወቅቱ በተለይም ባደጉት አገራት ጉልበትን ሸጦ ኑሮን የመግፋቱ አኗኗር እየተለወጠ የመጣበትና ዕውቀት ተኮር መሆኑን በማጣቀስ፤ በተለይ ወጣቶች ሕልማቸውን በትምህርት ሊደግፉ እንደሚገባ ይመክራሉ።
በተለይም የሌላ ሀገር ሰው ሆኖ በአደገው አገር ሥርዓት ውስጥ ሲኖር፤ በቂ የሚባል የትምህርት ደረጃ በቂ ነው ማለት አይደለም፤ ከዚያም ማለፍ አለበት።ዶ/ር ዕፀገነት አሰፋ፤ በፍሬድ ማየር - ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ የፋርማሲ ባለሙያ
ዶ/ር ዕፀገነት በቀጣዩ ክፍለ ዝግጅታችን ስለ ዩኒቨርሲቲ ምረቃቸውና የፋርማሲ ሙያ፣ የአሜሪካና የኢትዮጵያ ፋርማሲ አሠራሮችን፣ የቤት ግዢና ሽያጭ ሙያ ስምሪታቸውን አንስተው ይናገራሉ።
ተጨማሪ ያድምጡ
ዶ/ር ዕፀገነት አሰፋ፤ ፋርማሲ - የቤት ሽያጭና ግዢ