ውልደትና ዕድገት
ዐቢይ አየለ ውልደቱ አዋሬ - አዲስ አበባ ቤተ መንግሥት ጓሮ ነው።
ለቤተሰቡ አራተኛና የመጨረሻ ልጅ ነው።
ነፍስ ሳያውቅ ገና ጨቅላ ሳለ እናትና አባቱ ተለያዩ።
ዐቢይ አባቱ ዘንድ ቀረ።
ከፍ ሲልም ፊደል ቆጠራ ጀመረ።
ውስጡንም ማድመጥ ያዘ።
የቀለም ትምህርት
ዐቢይ የአንደኛና ሁለተኛ መለስተኛ የቀለም ትምህርቱን ጀምሮ ያጠናቀቀው በበዓታ ገዳም በኋላ መስከረም 2 ተብሎ በተጠራው ትምህርት ቤት ነው።
ጥቂት ዓመታት እንደተቆጠሩም ትልቅ ወንድሙ ወደ ውትድርና ገባ፣ እህቱ እናታቸው ዘንድ ሔደች፤ ሌላኛው ወንድሙ የፖሊስ ሠራዊት አባል ሆነ።
የመጨረሻ ልጅ መሆኑና እናቱ ዘንድ አለመሔዱ ከአባቱ ጋር ያለው ግንኙነት ከወላጅና ልጅ ዐልፎ የቅርብ ጓደኛሞች እንዲሆኑም አብቅቷቸዋል።
ከአባቱ ሃሳብን በነፃነት መግለጥ፣ ያልተረዳውን መጠየቅ፣ በጉዳዮች ላይ ደፍሮ መወያየትን ቀሰመ።
ለሥራ መታተርንም ያዘ።
የሥራ ዓለምና የጥበብ ሕይወት ጥሪ
ዐቢይ በቀን ሠራተኛነት ጉልበትን ሸጦ ራስን የመደገፍ ትርጉም ያወቀው ጡንቻዎቹ ሳይጠነክሩ፣ ትከሻው ሳይደነድን የ8ኛ ክፍል ተማሪ ሳለ ነው።
ቀጣሪው የሕንፃ ድርጅትም በቀን 1 ብር ከ 90 ሳንቲም ይከፍለው ጀመር።
እንደ ሥራው ሁሉ የጥበብ ፍቅሩ የተጠነሰሰው ገና የ7ኛ ክፍል ተማሪ ሳለ በቀበሌ ኪነት መድረክ ነው።
ከጥበብ ጋር በውል የተዋወወቀው ግና ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል በተማረበት የምኒልክ ትምህርት ቤት ነው።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ የአገዛዝ ሥርዓት ለውጥ ተካሔደ።
የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢሕዲሪ) መንግሥት በኢሕአዴግ የሽግግር መንግሥት ተተካ።
ETHIOPIA—1991: Addis Ababa, the Ethiopian People's Revolutionary Democratic Front (EPRDF) took over the Palace of the Ethiopian People's Democratic Republic (EPDR) Government. Credit: Francoise De Mulder/Roger Viollet via Getty Images
ጥቂት ቆይቶም፤ ራሱን ችሎ ዝነኛውን የኢትዮጵያ ብርቅ ተዋናይ ሞገስ ለማላበስ "የወጋየሁ ንጋቱ ቲአትር ክለብ"ን መሠረተ።
ክለቡ በርካታ አጫጭርና ረጃጅም ተውኔቶች ለመድረክ ለማቅረብ በቃ።
ሲልም፤ የኖርዌይ ሕፃናት አድን ድርጅት ጋር ተባብሮ ሕፃናትን በማሰልጠን አንድ ልዩ ትዕይንት አቀረበ።
የተውኔቱ ተሳታፊ ልጆች ተበትነው እንዳይቀሩ ጥያቄ ቀረበለት። ተስማማ።
የሰርከስ ኢትዮጵያ ኃላፊ የሆነ አንድ ካናዳዊም ታድሞ ዝግጅቱን ተመለከተ። ደስተኛነቱን ገለጠ።
ከሽሮ ሜዳ የተመረጡ አራት ወጣቶችን አክሎ ሌሎች ወጣቶችንም እንዲያሰለጥንለት ጠየቀ። ዐቢይ ጥያቄውን ተቀበለ።
በሰርከስ ኢትዮጵያ በቀን የ3 ብር ድጎማ ለመጓጓዣ ተቆረጠለት።
ለታክሲ 70 ሳንቲም እየከፈለ ቀሪውን ለኪሱ ማድረግ ጀመረ።
በወቅቱ የአባቱ ገቢ የጡረታ ገቢ በወር ከ50 ብር በታች በመሆኑ የተነሳ በቀን ሶስት ጊዜ መብላት ቀርቶ አንዴም ቀምሶ ለማደር ይቸገር ለነበረው ዐቢይ ከመጓጓዣ ተራፊው ገንዘብ ሁነኛ መደጎሚያ ሆነው።
የዐቢይ ብርቱ ፍላጎትና ሕልም የራሱን ቲያትር እየተዘዋወረ ማሳየት እንጂ በሰርከስ ዓለም መዝለቅ አልነበረም።
ሰርከስ ኢትዮጵያ ግና ኮምፒዩተር በዓይኑ እንኳ አይቶ የማያውቀውን ዐቢይ ከኮምፒዩተር፣ ሲዲና የድምፅ ቴክኖሎጂዎች ጋር አስተዋወቀው።
ሰርከስ ኢትዮጵያም በዐቢይ ባለ አንድ ክራርና ከበሮ 'ባንድ' ታጅቦ አዲስ አበባ በሚገኘው የኤርትራ ኤምባሲ ዝግጅቱን አቀረበ።
ድንቅ ተባለ።
የትዕይንቱ ትሩፋት ዐቢይን ከቀን የሶስት ብር ተደጓሚነት ወደ 400 ብር ደመወዝተኛነት አሸጋገረ።
የዐቢይ ትረካ በእዚህ አልተቋጨም።
በቀጣዩ ክፍለ ዝግጅታችን ዐቢይ እንደም አገር ለቅቆ ለመውጣት እንደበቃና ከደርዘን በላይ ከሆኑ የሰርከስ ኢትዮጵያ አባላት ጋር አውስትራሊያ ውስጥ ጥገኝነት ለመጠየቅ እንደበቁ ያወጋል።