"ከ30 የሰርከስ ኢትዮጵያ አባላት ውስጥ 15ታችን አውስትራሊያ ጥገኝነት ጠይቀን ቀረን" ዳይሬክተር ዐቢይ አየለ

Abiy Asylum.png

Abiy Ayele with Circus Ethiopia Band playing Kirar (L). Credit: A.Ayele and SBS Amharic

የቲአትርና ፊልም ዳይሬክተር ዐቢይ አየለ፤ በቀዳሚ ክፍለ ዝግጅታችን ስለ ትውልድና ዕድገቱ፣ የቀለም ትምህርትና የጥበብ ዕውቀት ቀሰማውን ከሰርከስ ኢትዮጵያ መቀላቀሉ ጋር አሰናስሎ አንስቷል። በሀገረ አውስትራሊያ የጥገኝነት ጥየቃው ውሳኔውን አስከትሎ ያወጋል።


የባሕር ማዶ ኑሮ ዕሳቤ

ዐቢይ ከኢትዮጵያ ወጥቶ ለመቅረት ከመወሰኑ በፊት ከቡድኑ ጋር የሰርከስና ሙዚቃ ትዕይንቶችን በተለያዩ አገራት አሳይቶ ወደ ሀገር ቤት ተመልሷል።

ለመጀመሪያ ጊዜ ለሙያዊ ተልዕኮ ባሕር የተሻገረው የሰርከስ ኢትዮጵያ አባል በሆነ በዓመቱ ለ13 ቀናት ወደ ሆላንድ በመጓዝ ነው።

በወቅቱም ዝግጅቶቻቸውን ለንግሥቲቱና በአምስት የተለያዩ ከተሞች ተዘዋውረው ትዕይንቶቻቸውን አሳዩ።

በቀጣይነትንም ለአራት ጊዜያት ያህል በየዓመቱ በክረምት ወራት ዝግጅቶቻቸውን ባሕር ማዶ አቅርበዋል።

አሜሪካን አገር ሔዶ ለመኖር የ Diversity Visa (DV) ፕሮግራም ዕድል ቢደርሰውም ለባዕድ ሀገር ኑሮ ሥነ ልቦናዊ ዝግጅት አልነበረውምና 'እምቢኝ' ብሎ ቀረ።

በምትኩ ሰርከስ ኢትዮጵያ ውስጥ የዐቢይ ደመወዝ ጨመረ፤ የጥቅም ግጭት ቢኖርበትም እንኳ ዳይሬክተርና የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል ሆነ።

ሆኖም፤ ከአምስት ዓመታት ቆይታ በኋላ ሰርከስ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው የአሠራር ሂደት አለመግባባት ሳቢያ ለመሰናበት አሰበ።

ግና ከሥራው ተሰናብቶ ሀገር ውስጥ ቢቀር የሚገጥመው ዕድል የቲአትር ቤቶች ተቀጣሪ መሆኑን ልብ ሲል ልቡ ወደ ባሕር ማዶ አሻቀበ።

በመሃሉ፤ ሰርከስ ኢትዮጵያ አውስትራሊያን ጨምሮ በስድስት ሀገራት ትዕይንቶቹን ለማሳየት ወጣ።

ጥገኝነት ጥየቃ

ዐቢይ ከሰርከስ ኢትዮጵያ ጋር አውስትራሊያ - አደላይድ ከተማ ገባ።

አብሮ አደግ ጓደኞቹን ሳያስበው አገኘ።

አውስትራሊያ ለመቅረት መወሰኑን ነገራቸው።

እንደ ውስጥ አውቅነታችው አላደፋፈሩትም።

ከቶውንም፤ ጥሩ የሙያ ክህሎት፣ ከፍ ያለ ክፍያና ከሀገር እየወጡ የመግባት ዕድሎች እያሉህ የስደት ኑሮን መምረጥ 'አይበጅም' ሲሉ ምክረ ሃሳባቸውን ቸሩት።

ዐቢይ ግና በውሳኔው ፀና፤ በጄ አልል አለ።

አብሮ አደጎቹ ውሳኔውን ተቀበሉ።

እንደ ሀገር ልጅነታቸው 'መልካም ዕድል' ተመኙለት።

ባዕድ ሀገር ገብቶ አስጠልሉኝ ማለት በዋዛ 'እንዳልክ' የሚሰኝበት አይደለምና ከደርዘን በላይ ከሆኑ የሙያ አጋሮቹ ጋር ጥገኝነት ጠየቁ።

አቤቱታቸው ለኢሚግሬሽን ባለስልጣናት ውሳኔ ቀረበ።

የቲአትርና ፊልም ዳይሬክተር ዐቢይ አየለ፤ በቀጣይና የመደምደሚያ ግለ ታሪኩ የጥገኝነት ጥየቃ ሂደቱን ምላሽና የወደፊት ውጥኖቹን አንስቶ ያወጋል።





Share