SBS Examines: አውስትራሊያ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የወሲብና ወሲባዊነት ትምህርት የሚሰጠው ስለምን ነው?

Busy school yard, pavement or footpath. Legs in motion

From pre-school to year 12, sexual education is part of the school curriculum in Australia. Source: Getty / Lincoln Beddoe

የትምህርት ቤቶች ወሲባዊ ትምህርት አወዛጋቢ ነው፤ ይሁንና ጠበብት የወጣቶች ስለ አካሎቻቸው፣ ማንነቶቻቸውና ጤናማ ግንኙነት መማር ወሳኝ እንደሁ ይናገራሉ። የተወሰኑ ወላጆች ስጋት ያደረባቸው ስለምን ነው?


እንደ ኢ-ሊን ቻንግ፤ በሥነ ቤተሰብ አውስትራሊያ ጤና ማስተዋወቅ ሥራ አስኪያጅ አባባል ሁሉን አቀፍ ወሲባዊ ትምህርት ዘርፈ ብዙ ጠቃሚ ርዕሰ ጉዳዮችን እንደሚሸፍን ሲገልጡ፤

"ስለ ወሲብ፣ በወሲብ ስለሚተላለፉ በሽታዎችና የፅንስ መከላከያ ብቻ አይደለም። ስለ ይሁንታ፣ ግንዛቤ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ ላይ መድረስና ያም ምን እንደሚመስል መረዳት ነው" ይላሉ።

ሆኖም ወላጆች ልጆቻቸው ወሲብን አስመልክቶ ምን እንደሚማሩ ስጋት ያላቸው መሆኑን አልሸሸጉም።

"የተለያየ መደብ ካላቸው ወላጆች ዘንድ በርካታ ስጋቶች መኖር የተለመደ ነው"

"ለምሳሌ፤ እንዲህ ዓይነቱ ትምህርት ልጄን ሔዶ ወሲብ እንዲፈፅም ያደርገዋል?" በማለት እንደሚጠይቁ ወ/ሮ ቻንግ ለ SBS Examines ተናግረዋል።

ወ/ሮ ቻንግ ወሲባዊነትን የተላበሰ ትምህርት በተማሪዎች ልክ የተመጠነ ሊሆን እንደሚገባው፤ በጣሙን ጥንቃቄ የሚሹ ጉዳዮች ሲሸፈኑ ባሕላዊነትን ያካተቱና ከዕድሜ ጋር መጣኝ በሆነ መንገድ መሆን እንዳለበትና ሆኖም መረጃን መሸሸግ እንደማይገባ ሲያስረዱ፤

"የእያንዳንዱን ግለሰብ ባሕላዊና ሃይማኖታዊ መሠረት የአተያዮቻቸው አካል ስለሆነ፤ ከተሳታፊዎች ፍላጎቶች ጋር አብሮ የሚሔድ መሆን አለበት" ይላሉ።

በኢድዝ ኮዋን ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ክፍል ገዲብ መምህር የሆኑት ዶ/ር ዴቪድ ሮድስ፤ አውስትራሊያ ውስጥ የወሲብ ትምህርት “ስኬትና ክሽፈትን” የተላበሰ ነው ባይ ናቸው።

ሥርዓተ ትምህርቱ አሻሚና ለይሆናል ትርጓሜ የተጋለጠ ነው ስለሚለው ዕሳቤያቸው ሲያስረዱም፤

"አውስትራሊያ ውስጥ ሁሉንም ተማሪዎች ወይም ወጣቶችን የምናስተምረው ተመሳሳይ ነገሮችን አይደለም፤ እናም ተመሳሳይ የሆኑ ቁሶችና መረጃን እንዲያገኙ አናደርጋቸውም" ይላሉ።

ወጣቶች ስለ ወሲብና ወሲባዊነት ጥያቄዎቻቸው የሚሹትን ምላሾች ካላገኙ ወደ ሌላ ቦታ ይመለከታሉ፤ እናም አግባብነት ወደ ሌላቸው የወሲብ ድረገፆች ወይም መነጋገሪያዎች ሊያመሩ ይችላሉ ሲሉም አክለዋል።

ከወጣቶች ጋር ወሲብን አስመልክቶ ያለው ልማዳዊ አተያይ እንዳለ ሆኖ፤ ሁሉን አቀፍ ወሲባዊ ትምህርት ወሳኝ እንደሁ ሲያመላክቱም፤

"እኒህ ትምህርቶች ለአንድ ግለሰብ ማንነትና ጤናማ ግንኙነቶች ለመመሥረት ወሳኝ ናቸው ... በእኛ ክብካቤ ስር ያሉ ልጆችን ፍላጎቶች ልናስተናግድ ግድ ይለናል" ብለዋል።



Share