ውልደትና ዕድገት
ተስፋዬ ገብረሃና ውልደቱ ወላይታ ሶዶ - ቦዲቲ፤ ዕድገቱ መሃል ፒያሳ "መንዜ ሠፈር" ነው።
ዕድሜው 10 - 11 እስኪደርስ ያደገው የ5 ወር ልጅ ሳለ ዕትብቱ ከተቀበረባት ቦዲቲ ወደ መንዜ ሠፈር ይዘውት ከመጡት እናቱ ጋር ነው።
ከ10 ዓመት በኋላ እናቱ ወደ ቀዬያቸው መመለስ ሻቱ።
ተስፋዬና የ7 ዓመት ወንድሙ አዲስ አበባ መቅረትን መረጡ።
እናቱ የቦዲቲ ተስፋዬና ታናሽ ወንድሙ የመሃል አራዳ ነዋሪዎች ሆኑ።
ጎረቤቶቹ አሳዳጊዎቹ ሆኑ።
ትምህርቱን ቀጠለ።
የመንዜ ሠፈር ጎረቤት ነው ያሳደገኝ።ተዋናይ ተስፋዬ ገብረሃና
ትምህርትና ተውኔት
ከ1ኛ እስከ 3ኛ ክፍል አፍሪካ አንድነት ትምህርት ቤት ተማረ።
ከ4ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያለ ትምህርቱን በዳግማዊ ምኒሊክ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አጠናቀቀ።
ከመድረክ ትወና ጋር የተዋወቀውም እዚያው ነው።
9ኛ ክፍል ሳለ የትምህርት ቤቱን ድራማ ክበብ በመቀላቀል።
የመጀመሪያ የመድረክ ትወናው "ሳይቃጠል በቅጠል" አጭር ድራማ የሶስት ልጅ አባት የሆኑት አቶ አንዳርጌ ገፀ ባሕርይ ነው።
የድራማው ደራሲና አዘጋጅ ተስፋዬን ለመድረክ ያበቁት መምህር መኮንን ናቸው።
ትወናው አድናቆትን አተረፈ።
የስኬት ጣዕም የተስፋዬን የጥበብ ፍቅር አሳደገ።
አፍታም ሳይቆይ "የዳግማዊ ምኒሊክ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ የድራማ ክበብ" ሊቀመንበር ሆነ።
የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት የወጣቶች ቲአትር ቡድን ዳግማዊ ምኒሊክ ትምሀርት ቤት መጥቶ "ኮሌታው" የሚል አጭር ድራማ አሳየ።
"ኮሌታው" የተስፋዬን ቀልብ ገዛ።
ከደራሲው ጋር ተዋወቀ።
ቲአቲሩን አስፋፍቶ ለመፃፍ ፈቃድ አገኘ።
በተስፋዬ ዳብሮ የተፃፈው "ኮሌታው" ተጋባዥ ስመጥር አንጋፋ የተውኔት ተጠባቢዎች በተገኙበት ለመድረክ በቃ።
ጋባዡ ተስፋዬ ነበር።
ከተጋባዦቹ መካከል ተስፋዬ በታላቅ አርአያነት ተውኔቶቹን ቃል በቃል ሸምድዶ ያጠናለት ጌትነት እንየው ይገኝበታል።
ጥቂት ቆይቶ፤ ተስፋዬ የበጎ ፈቃደኛነት የአጭር ድራማ ትወና ግብዣ ደረሰው።
ጋባዡ ጌትነት እንየው ነበር።
ተስፋዬ ግብዣውን በታላቅ ደስታና ከበሬታ ተቀበለ።
በጋባዡ ጌትነት የተዘጋጀውን "ዘለለኝ" አጭር ተውኔት የፖሊስ መኮንን ገፀ ባሕሪይ ተላብሶ ብሔራዊ ቲአትር መድረክ ላይ ተጫወተ።
ድንቅ ተሰኘ።
ገፀ ባሕሪዩን ለስድስት ጊዜያት ደጋግሞ ብሔራዊ ቲያትር መድረክ ላይ ተወነ።
ለእያንዳንዱ የመድረክ ትወናው 25 ብር ተከፈለው።
የ150 ብር ጌታ ሆነ።
ለ 'አሉላ ቲአትር ክበብ' አባልነት በቃ።
በለስ ቀንቶት ወጣት ተዋንያንን ለታላላቅ የጥበብ መድረክ ሰውነት በማብቃት በኪነ ጥበቡ ዓለም አሻራውን ትቶ ያለፈውና እስካሁንም የሚታሰበው አንጋፋው ተዋናይ፣ ደራሲና አዘጋጅ መላኩ አሻግሬ ዓይን ውስጥ ገባ።
መላኩ - ተስፋዬን የጥበብ ልጁ አደረገ።
ከባልደረቦቻቸው ጋር ሆነው በየክፍለ አገሩ እየተዘዋወሩ ተውኔቶቻቸውን ለሕዝብ ማቅረብ ያዙ።
በክፍለ አገር የትወና ጉዞው ከወጪ ቀሪ 680 ጥሬ ብር በእጁ ጨብጦ አዲስ አበባ ገባ።
"ቱጃር" ሆነ።
ተዋናይ ተስፋዬ ገብረሃና፤ በቀጣዩ ክፍለ ዝግጅታችን ከተውኔት ባልደረቦቹ ጋር እንደምን ቲአትርን ከከተማ እስከ ጦር ካምፕ ለመድረክ እንዳበቁና ከኢሕዲሪ በኢሕአዴግ መተካት ወዲህ ያለውን የጥበብ ሕይወት ጉዞውን ነቅሶ ያወጋል።