"አውስትራሊያውያን ሙዚቀኞች አውስትራሊያ ውስጥ ባንድ ፈጥረው የኢትዮጵያን ሙዚቃ እንዲጫወቱ በጎ ተፅዕኖ ማሳደር ችለናል" ኪቦርዲስት ዳንኤል አጥላው

Daniel Seifu Atlaw.jpg

Keyboardist Daniel Atlaw. Credit: D.Atlaw

ዳንኤል አጥላው፤ በሜልበርን - የአውስትራሊያ ነዋሪ ነው። በለጋ የልጅነት ዕድሜ ያደረበት የሙዚቃ ፍቅር በያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ውስጥ አልፎ ከትሮምቦን እስከ ኪቦርድ ተጫዋችነት አድርሶታል። ከአገር ቤት እስከ ባሕር ማዶ ባሉ መድረኮችም ታዳሚዎቹን በኪቦርድ ቅላፄ ሐሴትን አላብሷል። በብሔራዊ ቲአትር የዘመናዊ ሙዚቃ ክፍል ኃላፊም ሆኖ አገልግሏል።


አንኳሮች
  • ከካዛንቺስ እስከ ሜልበርን
  • የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ጅማሮና ሂደት
  • የኢትዮጵያን ሙዚቃ ለአውስትራሊያውያን የማስተዋወቅ እንስቃሴዎችና ስኬቶች
ዳንኤል አጥላው፤ ከአዲስ አበባ ካዛንቺስ ተንስቶ የኪቦርዱን ወስዶ-መላሽ ድምፅ በሜልበርን መድረኮች ላይ ለማናኘት የበቃው በጽጌረዳ ፍራሽ ላይ ተረማምዶ አልነበረም።

ወላጆቹ እንደ ወቅቱ በርካታ ኢትዮጵያዊ ቤተሰብ ከሙዚቃ ይልቅ ወደ ቀለም ትምህርቱ አተኩሮ 'አንቱ' የተሰኘ ልጅ እንዲወጣላቸው ይሹ ነበርና ከመነሻው ድጋፋቸው ነፍገውት ነበር።

ተስፋ ቆርጦ ከሙዚቃው ይልቅ ወደ ቀለሙ እንዲመለስ የአውቶቡስ መሳፈሪያ ሳንቲሞችን አልሰጥ ብለውታል። ዳንኤልም በእግሩ እየተጓዘ ወደ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ተመላልሷል።

የሕይወት ነዳጁ የሙዚቃ ፍቅሩ ነበር። እናም በየቀኑ ከአንበሳ አውቶቡስ ጋር ባለ ጎማና እግረኛ ሆነው የሻጉራ እየተያዩ አያሌ ቀናት አስቆጠሩ።

ዳንኤል በሙዚቃ ትምህርቱ ተሰጥዖው፣ ትጋቱና ፈጥኖ ቀሳሚነቱ ተሰናስለው ውጤቱ ያማረ ለመሆን በቃ።

የቤተሰቡንም ልብ አሸንፎ ይሁንታቸውን ተቸረ።

ሲልም፤ በብሔራዊ ቲአትር መድረከኛነት ብቻም ሳይወሰን ለዘመናዊ ሙዚቃ ክፍል ኃላፊነትም በቃ።

የሕይወት ጉዞው እትብቱ በተቀበረባት መዲናይቱ አዲስ አበባ አልተወሰነም።

የሕይወት ኮከቡ ወደ አውስትራሊያ መርታ፤ በጢያራ ውቅያኖስን አሻግራ ለሜልበርን ነዋሪነት አበቃችው።

'ሙዚቃ የዓለም ቋንቋ' እንዲባል፤ ባሕር ማዶኛ በመሆኑ የኪቦርዱ ልሳን አልተዘጋም።

ከቶውንም አገርኛ ቅላፄው የአገረ አውስትራሊያን ጆሮ ለመሳብ ቻለ።
Daniel Atlaw Keyboard.jpg
Daniel Atlaw. Credit: D.Atlaw
ዳንኤል፤ ሿሚ ሳያስፈልገው በጥረቱ ራሱን በአውስትራሊያ የኢትዮጵያ ሙዚቃ 'አምባሳደር' አደረገ።

ከአውስትራሊያውያን የጥበብ ሰዎች ጋር ተስማምቶ ስመጥር ኢትዮጵያውያን የሙዚቃ ሰዎችን በሜልበርን ታላላቅ የሙዚቃ መድረኮች ላይ ግዘፍ አስነሳ።

ማኅሙድ አሕመድ፣ ዓሊ ቢራ፣ ዓለማየሁ እሸቴ እና እንዳልካቸው የኔይሁን (2PAC) በፈረቃ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ለአውስትራሊያውያን እነሆኝ አሉ።
Dani and Ethiopian artists.jpg
From L-R: Daniel Atlaw, Ali Bira, Mahamud Ahmed and Birgitta Åström (wife of Ali Bira) in Melbourne, Australia. Credit: D.Atlaw
ሰሞኑንም ከኖቬምበር 9 - 14 / ከጥቅምት 30 - ኅዳር 5 በሶስት የተለያዩ የሜልበርን መድረኮች የምዕራባውያኑንና የኢትዮጵያን ረቂቅ ሙዚቃዎች አዋድዶ ለማቅረብ ስንዱ ሆኖ ያለው ፒያኒስት ግርማ ይፍራሸዋም ታካይ ሆኗል።
Girma Yifrashewa.jpg
Pianist Girma Yifrashewa. Credit: D.atlaw

Share