ብፅዓትና ተስፋዬ
ሥፍራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቲአትር ቤት ነው።
ያኔ ድምፃዊት ብፅዓት ድምፅና ምስሏ በዘፈኖቿ ታጅበው የኢትዮጵያ ሬዲዮ የአየር ሞገድ፣ የቴሌቪዥን ሳተላይት ስርጭትና ካሴቶች በየቴፑ የሞሉበት ጊዜ ነው።
ተስፋዬም መድረክ ላይ ግዘፍ መንሳት የጀመረበት ወቅት ነው።
የዝና ደረጃቸው በየዘርፉ እንዳለ ሆኖ።
እናም ዕጣ ፈንታ አገናኘቻቸው።
ተዋወቁ። ተቀጣጠሩ።
በሙያ ባልደረባነት ሳይሆን፤ በተቃራኒ ፆታ ስህበት።
ግብዣ
ተስፋዬ ብፅዓትን ጋበዘ።
ኪሱ ውስጥ የነበረችው ግና 5 ብር ናት።
መላ አበጅቶ 15 ብር ከወዳጁ ተበደረ።
አምስቷ 20 ብር ደረሰች።
የግብዣ ወጪውን አሰላ።
አንድ ቋንጣ ፍርፍር 2 ብር ከ50 ሳንቲም፤ አንድ ብርጭቆ ድራፍት ቢራ 1 ብር ከ35 ሳንቲም።
20 ብሯ እንኳን ለአንድ እንግዳ ሞልታ ተርፋ ጎረቤቶቹንም ጭምራ ልትጋብዝ እንደምትችል አወቀ።
ዲታነት ተሰማው።
በልበ ሙሉነት ከብፅዓት ጋር በቀጠሯቸው ሰዓት ተገናኙ።
እንዳሰበው ሳይሆን ቀረ። ጋባዡ ተስፋዬ ተጋባዥ ሆነ።
በእግር ወይም በታክሲ ሳይሆን በብፅዓት የግል መኪና ከአንድ ትልቅ ሆቴል የምግብ አዳራሽ ገቡ።
በኮምፒዩተር ተለቅሞ የታተመ የምግብ ዓይነት ዝርዝር ተሽሞንሙኖ ቀረበ።
የ2 ብር ከ 50 ሳንቲም የቋንጣ ፍርፍር ግና ዝርዝሩ ውስጥ የለም።
በምትኩ ውድ የሀገር ባሕል ምግብ ቀረበ።
ወይን ተንቆረቆረ።
ገበታ ከፍ አል። ሂሳብ መጣ።
20 ብር ኪሱ ውስጥ ያለችው ተስፋዬ ለመክፈል ተግደረደረ።
የምግቡና መጠጡ ሂሳብ ከ500 ብር በላይ ሆነ።
የተስፋዬን የሶስት ወር ደመወዝ ሊሞላ 50 ብር ጉዳይ።
ማዕድ መቋደሳቸው የመጀመሪያውም የመጨረሻውም ሳይሆን ቀረ።
ፍቅር ተዋናዩንና ድምፃዊቷን አዋሃደ።
አንዳቸው በአንዳቸው ልብ ውስጥ መኖር ጀመሩ።
ዐልፎም፤ የፍቅር አብራክ ክፋይ ሴት ልጃቸውን "ፍቅር" ብለው ለመሰየም በቁ።
ሲልም፤ 26 የባልና ሚስት ዓመታትን አስቆጠሩ።
አሁን ለአለሁበት ደረጃ የበቃሁት፤ ብፅዓት ሕይወቴ ውስጥ በመግባቷ ነው።ተዋናይ ተስፋዬ ገብረሃና
ተስፋዬ ዛሬም ድረስ ከቴክኖሎጂ አመጣሹ ትወናዎች ይልቅ የመድረክ ተውኔትን ይመርጣል።
ተስፋዬ ግለ ታሪኩን በቀጣዩ ክፍለ ዝግጅታችን ይደመድማል።