“የአማራውን ሕዝብ ሌላው እንዲጠራጠረው፤ ይኼ ትውልድ ዕዳ እንዲከፍልና የበዳይነት ስነ ልቦና እንዲሸከም ተደረጎ ቆይቷል። የትርክት ዕረቃ መካሄድ አለበት” አባ መላ

DPM Demeke Mekonnen.jpg

Outgoing Ethiopia's Deputy Prime Minister and Minister for Foreign Affairs Demeke Mekonnen. Credit: EPO

ምልሰታዊ ምልከታ፤ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን (አባ መላ) በ2011 ያቀረቡት ይሥራ መልቀቂያ ተቀባይነት ባያገኝም ጥር 26 / 2016 ግና ከሁለቱም መንግሥታዊ የሥራ ኃላፊነታቸው ለቅቀዋል። መጠይቃችንን ያቀረብነውና አተያያቸውን ያጋሩን ባሕር ዳር ከተማ ነው። የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) 12ኛ መደበኛ ድርጅታዊ ጉባኤን (መስከረም 17-21/2011) በከፈቱና አምስት አሠርት ዓመታትን የተሻገሩባት ዕለተ ልደታቸውን ባከበሩባት የመስቀል በዓል ማግሥት። ብአዴን ወደ አማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ሳይለወጥ በፊት።


ውይይታችንን ያካሄድነው የዓባይ ወንዝ ምንጭ በሆነችውና በእምቦጭ ሳቢያ ጤናዋ ታውኮ ባለችዋ የጣና ሐይቅ ዕቅፍ ውስጥ ሞገስ ተላብሶ በቆመው Blue Nile ወይም Avanti ሆቴል ነው።
Blue Nile Hotel.jpg
Blue Nile Resort Hotel. Credit: SBS Amharic
ወቅቱ አገሪቱ አስደማሚ በሆነ የለውጥ ውቅያኖስ ላይ እየቀዘፈች፣ በሕዝብ ልብ ውስጥ ብሩህ ተስፋ ገንኖና ከአመራር አካላቱ ፊት ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶች ተደቅነው ያሉበት ነውና መጠይቃችንን የጀመርነው፤


“ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ ለምን አስፈለገ? ለውጡ ከየት ተንስቶ የት እንዲደርስ ነው ትልማችሁ?” በሚል ነው።


አፈፍ ብለው ግና በሰከነ አንደበት የገለጡት፤

ባለፈው ሩብ ክፍለ ዘመን ማለፊያ ሥራዎች ቢሰሩም፤ ኅብረተሰቡ የሚጠብቀው የዕድገትና የለውጥ ጉዞ በቂ ሆኖ አለመገኘት፣ ሕዝብን የማድመጥ ከፍተኛ ጉድለት መኖር፣ በወረቀትና ምድር ላይ ያለው ዕውነታ አለመጣጣም፣ አንድ አራተኛው የአገሪቱ ሕዝብ በድህነት ወለል ላይ መኖር፣ አንዱን ጠላት አንዱን ወዳጅ አድርጎ መፈረጅ፣ ያለፉትን ሥርዓታት እያወገዙ እዚያው ውስጥ መገኘት አስባብ ሆኖ ሕዝባዊ ግፊት በመፍጠር፤ ኢሕአዴግን ለተሃድሶ፤ አገሪቱን ወደ አዲስ የለውጥ ምዕራፍ እንደመራና ሲልም፤ የአመራርና የአቅጣጫ ለውጥ ማስከተል መቻሉን በማመላከት ነበር የቁጥር ሁለት ወንበርተኛ አተያያቸውን ያጋሩን።
DPM SBS.jpg
Deputy Prime Minister Demeke Mekonnen. Credit: SBS Amharic
አስከትለንም፤ “እኒህን ችግሮች ለመረዳት እንደምን ከሁለት አሠርት ዓመትታ በላይ ወሰደባችሁ?” ብለን ጠየቅን።


“አንጻራዊ የሆኑ የጤና፣ የትምህርትና ባለ ሁለት አሃዝ የምጣኔ ሃብት ዕድገቶች የመጨረሻው የውጤት ጫፎች ሆነው እየተወሰዱ፤ የጎደለውንና ሕዝቡ የሚለውን ለማዳመጥ ከፍተኛ ጉድለት ነበረብን” ሲሉ መለሱ።


ያለፈውን የአመራሩን የሩብ ክፍለ ዘመን ከላይ ወደ ታች የግርዶሽ ምልከታ በትርክት አዋዝተው። ዝርዝሮችንም አክለው።


ባለፉት በርካታ ዓመታት ውስጥ ተበዳይ ከሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ አንዱ የአማራው ሕዝብ መሆኑንም አንስተዋል። ከትረካው ጀምሮ።


“የአማራውን ሕዝብ ሌላው እንዲጠራጠረው፤ ይኼ ትውልድ ዕዳ እንዲከፍልና የበዳይነት ስነ ልቦና እንዲሸከም እየተደረገ ትርክቶች ቆይተዋል። የትርክት ዕረቃ መካሄድ አለበት” ሲሉም የትረካ እርማት ግድ እንደሚል በአጽንኦት አስገንዝበዋል።


ከዘር ፖለቲካ ለመጽዳት፣ ብሔራዊ ማንነትንና አገራዊ አንድነት ለማጎልበት፤ ኢትዮጵያን ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ምቹ እንድትሆን ማድረግ እንደሚገባ ያላቸውን አመኔታ አጠንክረው የገለጡት ላፍታም ሳያመነቱ ነው።


ከአሜሪካውያኑ ፕሬዚደንቶች ሩዜቨልትና ሞንሮ ባልተቀዳ መልኩ።


በቀጣዩ ክፍል ሁለት ዝግጅታችን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እንደምን ከሥልጣን እንደለቀቁ፤ በመንበራቸው ዶ/ር ዐቢይ እንደተተኩ፤ ራሳቸውን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ለማሻገር እንዳልወደዱና ከሥልጣንም መውረድ እንዳልመረጡ፤ እንዲሁም፤ ስለምን "አባ መላ" እንደተሰኙ ያወጉንን ይዘን እንቀርባለን።

Share