“ያጎደልናቸው፤ ያጠፋናቸው ነገሮች አሉ። ይቅርታ መጠየቅ አለበት። ይቅርታ የምንጠይቅባቸው ጉዳዮች አሉ” ተሰናባች ም/ጠ/ር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

FM Demeke.jpg

Outgoing Ethiopia's Deputy Prime Minister and Minister for Foreign Affairs, Demeke Mekonnen, addressed the 78th United Nations General Assembly at UN headquarters in New York City on September 23, 2023. Credit: KENA BETANCUR/AFP via Getty Images

ምልሰታዊ ምልከታ፤ በክፍል ሁለት ቀጣይና መደምደሚያ ቃለ ምልልሳችን፤ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከመምህርነት ወደ ፖለቲካው ዓለም እንደምን ተስበው እንደዘለቁ፤ ወደ ቁጥር ሁለት የሥልጣን እርከን ላይ እንዴት እንደደረሱ፤ በምን ሳቢያ “አባ መላ” እንደተሰኙ፤ ባለፉት ሶስት የለውጥ ንቅናቄ ዓመታት የነበሩትን ፈታኝ ሁኔታዎች፣ የእሳቸውን መንታ መንገድ ላይ መድረስና ሚና አንስተው ይናገራሉ።


በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ “ትህትናና ቅንነት” የመልካም ስብዕና መገለጫ ናቸው። በፖለቲካው ዘርፍ ግና ዝንቅ ዕንድምታዎች አሏቸው። ሽኩቻ፣ መጠላለፍና አንጃ ገንነው ባሉበት የፖለቲካ መስክ “ትሁትና ቅን” ሆኖ መዝለቅ አዋኪ ነው። ይሁን እንጂ ስለ አቶ ደመቀ መኮንን ሲነሳ፤ “ትሁት” ፣ “ቅን” የሚሉ የባህሪይ ማጣቃሻዎች ይደመጣሉ።


አቶ ደመቀ ወደ ፖለቲካው መድረክ ብቅ ያሉት ገና በ20ዎቹ ለጋ የወጣትነት ዕድሜ ዘመናቸው በመሆኑ፤ አሁን ሰልፋቸው ከጎምቱ ፖለቲከኞች ተርታ ነው። ከዕድሜያቸው ግማሽ በላይ ለ26 ዓመታት በኢትዮጵያ የተለያዩ የፖለቲካ አመራር ዕርከኖች ላይ ቆይተዋል።


ከመምህርነት በቀጥታ የዘለቁት ወደ አማራ ክልል ከፍተኛ አመራር ነው። አነሳሳቸው ከክልል መንግሥቱ ቁጥር ሶስት የሥልጣን እርካብ ሲሆን፤ ምክትል ፕሬዚደንት፣ የብአዴን/አዴፓ ሊቀመንበር፣ የፌዴራል ሚኒስትርና ሲልም አሁን ካሉበት የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር መንበር ላይ ለመሰየም በቅተዋል።
DPM Mekonnen.jpg
Outgoing Ethiopia's Deputy Prime Minister and Minister for Foreign Affairs Demeke Mekonnen. Credit: Courtesy of PD
በዘመናዊ ፖለቲካ ራስን ለሕዝብ አዳምቆ መሸጥ ግድ በሚልበት ዘመን፤ ስለራሳቸው ለመናገር ቁጥብ ናቸው። በቅንጭቡም ቢሆን በእርሳቸው አንደበት ስለ ደመቀ መኮንን ማንነት እንዲነግሩን በማንሳታችን ግና ‘ከቤተሰብ ሕይወታቸው ጀምሮ ዕርቀ ሰላምን ማውረድ መውደዳቸውን፣ ሁሉንም ሰው እኩል የማየት፣ የማድመጥ፣ ነገሮችን አጣጥሞ ወደ መፍትሔ የመውሰድ ተሰጥዖዎቻቸው “አባ መላ” እንዳሰኟቸው’ ከአንደበታቸው ለማድመጥ በቅተናል።

የአጼ ምኒልክን ቀኝ እጅ ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ “ሀብቴ አባ መላ”ን ያስታውሷል።


ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ፤ አስተዳደጋቸው ከኦሮሞ፣ አገው፣ ሺናሻና የጉምዝ ተወላጆች ጋር በመሆኑ ለብዝሃነት ባይተዋር እንዳልሆኑ፤ ያም የኢትዮጵያን ዝንቅ ብሔረሰባዊ ገጽታና ምልከታዎች እንዲረዱ፤ በቀላሉ ከሰዎች ጋር ተግባብተውና ተከባብረው ለመኖር አዎንታዊ አስተዋጽዖ እንዳበረከተላቸው ይገልጣሉ።


በሶስቱ የለውጡ ጉዞ ዓመታት ውስጥ፤ አይነኬ የሚባሉ አስተሳሰቦችንና ተቋማትን መታገል፤ እንደ ብአዴን ሊቀመንበርነታቸውና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው የብአዴንን ፍላጎት ከፌዴራል ጋር አጣጥሞ መሄድ ፈታኝ እንደነበሩ፤ አቶ ለማና ዶ/ር ዐቢይ ሲመጡም በመመጋገብ አሁን ለተደረሰበት ደረጃ መብቃት መቻሉን በምልሰት ነቅሰው ያወጋሉ።

Abiy and Demeke.jpg
Ethiopia's Prime Minister Abiy Ahmed (R) speaks with Outgoing Ethiopia's Deputy Prime Minister and Minister for Foreign Affairs Demeke Mekonnen, during the launch of his green legacy initiative at a hall of the Prime Minister's office temporarily transformed into a green garden in Addis Ababa, Ethiopia, on May 18, 2021. Credit: AMANUEL SILESHI/AFP via Getty Images
ስለ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ሲያነሱም፤ “ትሁት፣ ብርቱ ሠራተኛ፣ ይበልጡኑ ወደ ቀለም ትምህርት የሚያተኩሩ...” ብለው በማንሳት፤ “ሥልጣን ይበቀኛል። እኔ የመፍትሔው አካል ልሁንና አገርን ልታደግ ማለት፤ በደም ሥልጣን ሲዘዋወር በነበረባት አገር ውስጥ ትልቅ ውርሰ አሻራ ሆኖ ሊወሰድ የሚችል ነው” ሲሉ ታሪክ የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በማለፊያ ሚዛኑ እንዲመዝናቸው ይሻሉ።

Haile and Demeke.jpg
Former PM Hailemariam Desalegn (L) and Outgoing Deputy Prime Minister and Minister for Foreign Affairs Demeke Mekonnen. Credit: PD
ስለራሳቸው ውርሰ አሻራ ግና የኢትዮጵያ ሕዝብ ተገቢ የሚለውን የታሪክ ሥፍራ ቢቸራቸው ይወዳሉ።
“ባለፉት 27 ዓመታት ያጎደልናቸው፤ ያጠፋናቸው ነገሮች አሉ። ይቅርታ መጠየቅ አለበት። ይቅርታ የምንጠይቅባቸው ጉዳዮች አሉ”
ተሰናባች የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን (አባ መላ)
የአገር ቁስል እንዲሽር፤ ጠባሳው እንዲደበዝዝ።
Kassa and Demeke.jpg
DPM Demeke Mekonnen (L), and Journalist Kassahun Seboqa (R). Credit: SBS Amharic




Share