ጭጋግ መሬት ቢረግጥ
ጸሃይ ብትሸፈን፣
አየሩ ቢታፈን፣
ኑሮ ረመጥ ቢሆን፣
ዙሪያው ገባው ሁሉ
ማቅ ለብሶ ቢዳፈን፡፡
ሳቄን ማን ከልክሎኝ፣
አልፎ ሂያጂነቴን
ጉዞዬን ማን ገቶኝ፣
እርቃኔንም ብሆን
የውስጤን ነጻነት እንደያዝኩት አለሁ
በውስጤ ሃብት አለኝ፡፡
አትሳቅ አትበሉኝ ... ሳቄ የቀረ ዕለት፣
የደኸየሁ እንደሁ ... በፈገግታ ንፍገት፣
ያኔ ነው የኔ ሞት፡፡
ጫማም አላቂ ነው
ከስር ተሸንቁሮ፣
ልብስም ይቀደዳል
ውሉ ተተርትሮ፣
ሁሉም አላፊ ነው
ያረጃል ያፈጃል
ትናንትም አርጅቶ
ጥንት ይባላል ዱሮ፡፡
አትሳቅ አትበሉኝ ... ሳቄ የቀረ ዕለት
የደኸየሁ አንደሁ ... በፈገግታ ንፍገት፣
ያኔ ነው የኔ ሞት፡፡
.............................
ጸደይ 2020