የኢትዮጵያ ንጉሣዊ በጎ አድራጎት ባለ አደራ ድርጅት ተመሠረተ

የኢትዮጵያ ንጉሣዊ በጎ አድራጎት ባለ አደራ ድርጅት (Royal Ethiopian Trust) ትርፍ አልባ ድርጅት መመሥረቱን በይፋ ያስታወቁት የኢትዮጵያ የዘውድ ምክር ቤት ፕሬዚደንት ልዑል ኤርሚያስ ሣህለ ስላሴ ኃይለ ስላሴ ሲሆኑ፤ ዋነኛ ተልዕኮውም የኢትዮጵያን ዘውድ ትዉፊትና ታሪክ ለማስቀጠል፣ የኢትዮጵያውያንን ባሕል ለማስተዋወቅና ሕዝቧንም በትምህርትና ምጣኔ ሃብት ለማበልፀግ መሆኑን ጥቅምት 1, 2024 ዓ.ም. ገልጠዋል።

Prince Ermias.jpg

His Imperial Highness Prince Ermias Sahle-Selassie Haile-Selassie, President of the Crown Council of Ethiopia. Credit: Crown Council of Ethiopia

የኢትዮጵያ ንጉሣዊ በጎ አድራጎት ባለ አደራ ድርጅት ዋነኛ መሠረታዊ ዓላማዎችና ትኩረት የሚያደርግባቸው የሥራ መስክና ዘርፎችም፤

1. ትምህርት

2. የሥራ ልምምድና ንግድ

3. የኢትዮጵያን ዘውድ ቅርስና ውርስ ማስጠበቅና

4. ለኢትዮጵያ ዘውድ ሁለንተናዊ ድጋፍ ማድረግ እንደሆኑ ተመልክቷል።


የኢትዮጵያ ዘውድ ምክር ቤት ፕሬዚደንቱ የበጎ አድራጎት ድርጅቱ ይፋ በሆነበት ወቅት ባደረጉት ንግግር፤

“የኢትዮጵያ ንጉሣዊ በጎ አድራጎት ባለ አደራ ድርጅት ከብዙ ድካምና ልፋት በኋላ በመቋቋሙ እጅግ ደስ ብሎኛል። ይህ ድርጅት እንዲቋቋም ከጎኔ ሳይለዩ ለደገፉኝና ለተባበሩኝ ሁሉ ከልብ አመሰግናለሁ”

"የኢትዮጵያን ጥንታዊ ታሪክ ከወደፊቱ ጉዞዋ ጋር ለማቆራኘት፣ የኢትዮጵያን ዘውዳዊ ዉርስና ቅርስ ለመጠበቅና ኢትዮጵያ አንድነቷን ጠብቃ ወደፊት እንድትራመድ በመላው ዓለም ከሚገኙ ደጋፊ ግለሰብና አጋር ድርጅቶች ጋር ለመሥራት እንሻለን” ሲሉ ተናግረዋል።

አያይዘውም፤ የኢትዮጵያ ንጉሣዊ በጎ አድራጎት ባለ አደራ ድርጅት ያቀዳቸውን ግቦች ለማሳካት እገዛ እንዲያደርጉ በንግድ ሥራና በጎ አድራጎት አገልግሎት ለብዙ ዓመታት ተሠማርተው የሥራ ልምድ ያካበቱ፣ ከንጉሣዊ ቤተሰብ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ጋር ቅርበትና ትስስር ያላቸውን ግለሰቦች በቦርድ አባላትነትና በአማካሪነት እንዲያገለግሉ መሾማቸውን ገልጠው፤ ምስጋናም አቅርበዋል።

ከበጎ አድራጎት ድርጅቱ በአገልጋይነት ተሿሚ የሆኑት ዲያቆን ሰለሞን ክብርዬ በበኩላቸው፤

“በአራቱ የሥራ ዘርፎች ላይ ትኩረት በማድረግ የኢትዮጵያ ንጉሣዊ በጎ አድራጎት ባለ አደራ ድርጅት ለሃገራችን ብልጽግና፤ ለባህላችን ክብርና ለኢትዮጵያ አንድነት ደጋፊና ቋሚ መሆኑን ያሳያል” ብለዋል።

Share
Published 3 October 2024 9:29pm
Updated 3 October 2024 9:34pm
By Kassahun Seboqa Negewo
Source: SBS

Share this with family and friends