ትውልድና ዕድገት
ለማ ክብረት ውልደቱ ሠንጋ ተራ፤ ዕድገቱ ሽሮ ሜዳ አሜሪካ ኤምባሲ አጠገብ ነው።
የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን ያጠናቀቀው በቀድሞ መጠሪያው "ቁስቋም" ትምህርት ቤት ነው።
ለመጀመሪያ ጊዜ በግብ ጠባቂነት የተሰለፈውም የሶስተኛ ክፍል ተማሪ ሳለ ነበር።
እርግጥ ነው፤ ቀዳሚ ተመራጭ ግብ ጠባቂ አልነበረም። ተጠባባቂ ነበር።
በዕለቱ የለማ ቡድን 3 ለ 0 ይመራ ስለነበር፤ ከግማሽ ክፍለ ጊዜ ጨዋታ በኋላ ተተክቶ ገባ።
ምንም ግብ ሳይገባበት ተጫውቶ ወጣ።
ከቁስቋም ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ገባ። የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሆኖ።
ከትምህርት ቤት እግር ኳስ ሜዳ ወደ ክለብ ግጥሚያ
ለማ ክብረት፤ ከሌሎች ሶስት የዕድሜ እኩዮቹ ጋር ሆኖ ወደ መብራት ኃይል ቡድን አመራ።
ሆኖም በቁመቱ እጥረት የመብራት ኃይል ታዳጊ ወጣቶች አሰልጣኝ ሳይቀበሉት ቀሩ።
ፊቱን ወደ በራሪ ኮከብ ቡድን አዞረ። ስልጠና ጀመረ።
ለለማ ክብረት ከሁሉም በላይ ሐሴትን ያላበሰው ግና የእሱ በራሪ ኮከብ ቡድን በቁመቱ ማጠር አሌ ካለው መብራት ኃይል ታዳጊ ወጣቶች ቡድን ጋር ሁለቴ ተጋጥሞ፤ ሁለቴም ማሸነፍ መቻሉ ነው።
እምብዛም ሳይቆይ የበራሪ ኮከብ ቡድን ፈረሰ።
ለማና ጓደኞቹ ተሰባስበው "የባሕር ትራንዚት" ቡድንን አቋቋሙ።
ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ለወጣትና ለዋናው ብሔራዊ ቡድን ተመረጠ።
ለማ ክብረት የብሔራዊ ቡድን ዋና በረኛ ሆኖ ለመሰለፍ የበቃው በዋዛ አይደለም።
በወቅቱ በርካታ ስመ ጥር ግብ ጠባቂዎች ነበሩና።
ትውስታው ትክክል ከሆነ ለመጀመሪያ ጊዘ በተጠባባቂ በረኛነት ያመራው ወደ የመን ነው።
ወደ ሀገር የተመለሰው በግብ ጠባቂነት ሳይሰለፍ ነው።
ግና የለማ ኮከብ በጥጥ ማኅበርና የእርምጃችን ግጥሚያ ማንፀባረቅ ጀመረች።
እሑድ ዕለት በሙሉ ጨዋታ አቻ - ለአቻ የወጡት ጥጥ ማኅበርና እርምጃችን ለአሸናፊ መለያ ማክሰኞ ምሽት ዳግም እንዲጋጠሙ ተወሰነ።
ተጫወቱ። ዳግም አቻ ወጡ።
በፍፁም ቅጣት ምት መለያየት ግድ ሆነ።
ለማ ክብረት ሁለት የፍፁም ቅጣት ምቶችን ከግብነት አዳነ።
እርምጃችን ጥጥ ማኅበርን አሸነፈ።
ድሉ የለማን ኮከብ ግብ ጠባቂነት አስመሰከረ።
ለማ ከአጥቂዎችና ቅጣት ምት መቺዎች ግቦችን አዳኝ ብቻም አልነበረም።
ግብ ጠባቂ ሆኖ ግብ ያስቆጠረባቸውም ጊዜያት አሉ።
ከአንድ እስከ 11 ያሉ ተጫዋቾች በሙሉ ለግብ ጠባቂ አደገኞች ናቸው፤ በረኛውም ግብ ሊያገባ ይችላል።ለማ ክብረት፤ የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን ግብ ጠባቂ
በሀገራችን የተጫዋቾች ሬኮርድ በወግ የማይያዝ በመሆኑ፤ ለማ ክብረት በትክክል ለምን ያህል ጊዜያት በብሔራዊ ቡድን ደረጃ እንደተጫወተ ዋቤ አይነቅስም።
በግምት ግና የወጣት ቡድኑን አክሎ፤ ለብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን እናት ሀገሩን ኢትዮጵያን ወክሎ ለ27 ጊዜያት ያህል መጫወቱን ይናገራል።
ጉዞ ወደ ሞሪሽየስ
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የብሔራዊ ቡድኑ ለአፍሪካ ዋንጫ ለሚያደርገው ውድድር ተጫዋቾችን መምረጥ ያዘ።
ክህሎቱን በግብር በማሳየትና የዝና ካባንም በመደረብ ላይ ያለው ለማ ክብረት ግና ሳይመረጥ ቀረ።
በውሳኔው ግር ተሰኘ።
ለማ ውሳኔውን "ይሁን" ብሎ አልተቀበል አለ።
ከቶውንም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጠንሳሽና መሪ ድንቁ አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ዘንድ ቀርቦ ቅሬታውን አሰማ።
አቶ ይድነቃቸው ጉዳዩን አስመረመሩ።
ሰበቡ ለማ "ፍራሹን ሲሸጥ መርካቶ ታይቷል" ከሀገር ከወጣ ሊጠፋ ይችላል የሚል ስጋት በማደሩ መሆኑ ታወቀ።
ለማ ፍራሹን አለመሸጡ ተረጋገጠ።
በሁለተኛው ወይም በሶሶተኛው ቀን ተጠራ።
ለብሔራዊ ቡድን መመረጡ ተበሰረለት።
ሞሪሽየስ ላይ በተካሔደው የአፍሪካ ዋንጫ ግጥሚያ ለአሸናፊ ቡድን መለያ ለሞሪሽየስና ኢትዮጵያ አምስት - አምስት የፍፁም ቅጣት ምቶች ተሰጡ።
ለማ የሞሪሽየስን አራቱን የፍፁም ቅጣት ምቶች መረብ ላይ እንዳያርፉ አዳነ። ኤርሚያስ ወንድሙና ሲሳይ ሳህሌ ሁለት ግቦችን አስቆጠሩ።
ግጥሚያው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን 2 ለ 1 አሸናፊነት ተጠናቀቀ።
የሕይወቱ አንፀባራቂ፣ አይረሴ ቀንንና ጨዋታ ያቺ ዕለት መሆንዋን ዛሬም ድረስ አውስትራሊያ ሆኖ ያነሳል።
ለማ ክብረት፤ በቀጣዩ ክፍለ ዝግጅታችን ከሞሪሽየስ ጥገኝነት ጥየቃ እስከ አውስትራሊያ የዳግም ሠፈራ ሕይወቱ ያወጋል።