"የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግፎ እዚህ አድርሶኛል፤ ከአውስትራሊያ የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ የምሻው 'አይዞህ' የሚል የሞራል ድጋፍ ነው" ለማ ክብረት

Lemma Kibret Pt II.png

Lemma Kibret, former Ethiopian National Football Team goalkeeper. Credit: L.Kibret

በቀዳሚው ክፍለ ዝግጅት የቀድሞው ዝነኛ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በረኛ ለማ ክብረት፤ ከውልደት እስከ ዕድገት፣ ከቁስቋም የሶስተኛ ክፍል እግር ኳስ ተጫዋችነት እስከ ብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂነት እንደምን እንደ ደረሰ አውግቷል። በቀጣዩ ትረካው ከሞሪሽየስ ጥገኝነት ጥየቃ እስከ አውስትራሊያ ዳግም ሠፈራ ያለ የሕይወት ጉዞውን ነቅሶ ያወጋል።


ከሞርሽየስ ወደ አውስትራሊያ

ለማ ክብረትን ጨምሮ ኤርሚያስ ወንድሙ፣ ሰለሞን ወንድሙና ሲሳይ ከበደ ሆነው ሞሪሽየስ ላይ ጥገኝነት ጠየቁ።

የሞሪሽየስ መንግሥት ለተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን አስተላለፋቸው።

ከደርዘን ወራት የስደተኛነት ቆይታ በኋላ በዳግም ሠፈራ የአውስትራሊያን ምድር ረገጡ።

አውስትራሊያም ሁለተኛ ሀገራቸው ሆነች።

ከሀገርና ከቀድሞ ክለቦቻቸው ቢርቁም፤ ሜልበርን ከተማ ላይ ሌላ ክለቦችን አግኝተው መጫወት ያዙ።

ምንም እንኳ ለበረኛ ሰፊ ዕድል ባይኖርም፤ ለማ ክብረት ሜልበርን ውስጥ እ.አ.አ እስከ 1997 ድረስ በሁለተኛ ዲቪዚዮን ደረጃ ለዘጠኝ ዓመታት ተጫውቶ አበቃ።

ከሜልበርን ነዋሪ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ - ኢትዮጵያውያን ልብና አዕምሮ ግና አልጠፋም።

ለማም ለወገኖቹ ፍቅርና ችሮታ ንፉግ አልሆነም።

ምስጋና

ለማ ክብረት በቅርቡ በሐኪሞቹ በአርትራይተስ ሕመም እንደተጠቃ ተነግሮታል።

ጉልበቶቹ ላይ ፅኑ ሕመም ይሰማዋል።

ኢትዮጵያውያኑ ይህንኑ አስበው ለጤናው ልገሳ፣ ለረጅም ጊዜ የሀገር ባለውለታነቱ ሞገስ ማላበሻ የሚሆን ልዩ መሰናዶ ላይ ናቸው።

ዝግጅቱ ለቅዳሜ ሰኔ 1 / ጁን 8 ቀን ተቆርጦለታል።
ለማ ክብረትም ዕሳቤውን ለነደፉት የቀድሞ የብሔራዊ ቡድን ባልደረባው አቶ ኤርሚያስ ወንድሙና አንጋፋ የማኅበረሰብ አባል አቶ ዓለም እሸትና ለተባባሪ አስተባባሪው የቪክቶሪያ የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ ማኅበር ልባዊ ምስጋናውን ከወዲሁ አቅርቧል።

በሀገረ አውስትራሊያ ሳይወሰንም "በዓለም ዙሪያ ላሉ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፤ ለሀገራችን ኢትዮጵያም ሰላምን እመኛለሁ" ብሏል።

Share