ሉናር አዲስ ዓመት ምንድነው እንደምንስ ነው አውስትራሊያ ውስጥ የሚከበረው?

ሉናር አዲስ ዓመት፤ እንዲሁም የቻይናውያን አዲስ ዓመት ተብሎ የሚታወቀው አንዱ የአውስትራሊያ ባሕል አካል ሆኖ ተዋድዷል። ከእስያ ውጪ ሲድኒ ውስጥ የሚካሔድ ትልቁ ክብረ በዓል መሆኑም አንዱ ዋቤ ነው።

Leão Vermelho no Ano Novo Lunar.jpg

Leão Vermelho no Ano Novo Lunar. Credit: AAP Image/Jeremy Ng

የዚህ ዓመት የሉናር አዲስ ዓመት የሚጀምረው ፌብሪዋሪ 10 / የካቲት 2 ነው።

አራት ዓይነት የአዲስ ዓመት ክብረ በዓሎች አሉ። የዝክረ መታሰቢያና ጸሎት ቀን፣ የአዲስ ዓመት ዋዜማ፣ የዳግም መገናኛና የስጦታ ቀን ናቸው።

የፋኖስ ፌስቲቫል ከመጀመሩ በፊት የፀደይ ፌስቲቫል ለአሥራ አምስት ቀናት ይዘልቃል።

በኒው ሳውዝ ዌይልስ ዩኒቨርሲቲ የቻይናና እስያ ጥናቶች ገዲብ መምህር የሆኑት ዶ/ር ፓን ዋንግ ስለ ዘመን ቆጠራውና አከባበሩ ሲናገሩ "ሉናር አዲስ ዓመት የሉናር ዘመን መቁጠሪያ መጀመሪያ ነው። የጨረቃን ዑደት ተከትሎም የቻይናውያን አዲስ ዓመት ወይም የፀደይ ፌስቲቫል ተብሎም ይጠራል"

"በዓሉ ቻይና ውስጥና እንደ ኮሪያ፣ ቬትናምና ጃፓንን በመሳሰሉ የምሥራቅ እስያ አገራትም ይከበራል" ብለዋል።

እንዲሁም፤ በማሌዥያ፣ ሞንጎሊያና በዓለም ዙሪያ ባሉ የዳያስፖራ ማኅበረሰባት ዘንድም ይከበራል።

የሉናር አዲስ ዓመት ከሺያ ወይም ሻንግ ሥርወ መንግሥት አንስቶ 4,000 ዓመታትን ያስቆጠረ ታሪክ እንዳለውም ዶ/ር ዋንግ አክለው ገልጠዋል።
Dragon.jpg
Credit: Getty Images/Kiszon Pascal

"የደቡባዊ ምሥራቅና ምሥራቃዊ እስያ ባሕሎችን የመማር ዕድል"

ዶ/ር ካይ ጃንግ ካንብራ በሚገኘው የአውስትራሊያ ብሔራዊ ዩኒቨርሲቲ የባሕል፣ ታሪክና ቋንቋ ትምህርት ቤት ዘመናዊ የቻይና ቋንቋ ፕሮግራም ላይ ተሰማርተው ያሉ ናቸው።

አውስትራሊያ ውስጥ የሚከበረው የሉናር አዲስ ዓመት ክብረ በዓል ከመላው ዓለም ለመጡ ሁሉ ስለ ቻይናውያን፣ ደቡባዊ ምሥራቅና ምሥራቃዊ እስያውያን ባሕሎች በአያሌው ለመማር ታላቅ ዕድል ነው እንደሆነ አመላክተዋል።

አያይዘውም፤

"ይህ ባሕላዊ ኩነት ረጅምና የበለፀገ ታሪክ፣ ተምሳሌያዊ፣ ትርጓሜ ተዛንቀው የተዋደዱበት ነው" ብለዋል።

የሉናር አዲስ ዓመት ማክበሪያ መንገዶች

የሉናር አዲስ ዓመትን የማክበር እንቅስቃሴዎች ማስዋቢያዎችን በየፈርጁ አድርጎ ማስጌጥን፣ በአዲስ ዓመት ዋዜማ ከቤተሰብ ጋር እራት አብሮ መመገብን፣ ቀይ ኤንቨሎፖችንና ሌሎች ስጦታዎችን ማደልን፣ ርችቶችን መተኮስ፣ የአንበሳና ድራጎን ዳንሶችን መመልከትን ያካትታሉ።

"ሉናር አዲስ ዓመት ከቤተሰብና ጓደኞች ጋር ተሰባስቦ ዓሣዎችን፣ ዱባዎችን በመመገብም ይከበራል" ሲሉ ዶ/ር ዋንግ ምግብ ከበዓሉ ጋር ያለውን ተያያዥነት ይገልጣሉ።

አያዘውም፤

"ቀይ ቀለም በጣሙን የመልካም ዕድል ምልክት ተደርጎ ይታሰባል። እናም አያሌ ቀይ ማስጌጫዎችን ትመልከታለችሁ፤ በቻይናውያን ልማዳዊ ሥርዓት የልጆች ዕድገትንና የአዲስ ዓመት ክብረ በዓል ማክበሪያ ተደርጎ ቀይ እኤንቨሎፕ ለልጆች በስጦታ ይቸራል" ብለዋል።
Chinese dancers.jpg
Chinese dancers perform during the Sydney Lunar Festival Media Launch at the Chinese Garden of Friendship in Sydney on February 9, 2021. Credit: AAP Image/Bianca De Marchi
አይሪስ ታንግ ያደገችው ቻይና ሲሆን አውስትራሊያን መኖሪያዋ ያደረገችው ከ20 ዓመታት በፊት ነው።

በአውስትራሊያና ቻይና በሚከበሩ ክብረ በዓላት መካከል ስላሉ ልዩነቶች ስትናገር ትውልድ አገሯ ውስጥ ከሉናር ክብረ በዓል ጋር የሚገጣጠም ለረጅም ጊዜ የሚከበር ሕዝባዊ በዓል መኖርን ተከትሎ፤ ቻይና ውስጥ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ዳግም ለመገናኘት ወደ ትውልድ ቀዬዎቻቸው እንደሚጓዙ ገልጣለች።

ታንግ እንደ ቻይና ሁሉ አውስትራሊያ ውስጥም ምግብ ለሉናር አዲስ ዓመት አከባበር አንዱ ጠቃሚ አካል እንደሆነ ስታነሳ፤

"በግሌ፤ እዚህ ካንብራ ውስጥ ብዙ ብዙ ምግቦችን በማዘጋጀት ከቤተሰቤና ጓደኞቼ ጋር አከብራለሁ። ከአዲስ ዓመት ዋዜማ አንስቶ በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠን በመቶዎች የሚቆጠሩ ዳምፕሊንግ እናዘጋጃለን"

"ከአንድ ማዕድ በላይ የሚሆን አዘጋጅና ማቀዝቀዣ ውስጥ አስቀምጣለሁ፤ በቀጣዮቹ የአዲስ ዓመት ክብረ በዓል ቀናት ለመመገብ" ብላለች።

የቻይናውያን ልማዳዊ የዘመን መቁጠሪያ

ምንም እንኳ ዘመናይት ቻይና የግሪጎሪያን ዘመን መቁጠሪያ ብትጠቀምም፤ እንደ ሉናር የቻይና አዲስ ዓመት፣ የፋኖስ ፌስቲቫልና ኪንግሚንግ ፌስቲቫልን ስለሚለይ ልማዳዊው የቻይና ዘመን መቁጠሪያ በስፋት ቻይና ውስጥና ባሕር ማዶ በሚኖሩ ቻይናውያን ዘንድ ይከበራል።

እንዲሁም ዶ/ር ዋንግ ሰዎች ለሠርግ፣ ለቀብር፣ ከሥፍራ ወደ ሥፍራ ለመጓዝ ወይም ለአዲስ ንግድ መጀመሪያ ቀናት እንደምን ልማዳዊውን የቻይናውያን ቀናት ስየማ ተከትለው እንደሚመርጡ ይገልጣሉ።
የቻይናውያን ልማዳዊ ዘመን መቁጠሪያ ከጨረቃና ፀሐይ ጋር ተያያዥ ነው። የተቀመረው በጨረቃና ፀሐይ እንቅስቃሴ በመሆኑ የጨረቃን የምድር ዙሪያና የመሬትን የፀሐይ ዙሪያ ምሕዋር በዕሳቤ ያካተተ ነው።
ዶ/ር ዋንግ "በእዚህ የዘመን ቀመር የወር መጀመሪያ የሚወሰነው በጨረቃ የታይታ ምዕራፍ ነው። በመሆኑም በአብዛኛው የሉናር ዘመን መቁጠሪያዎች የወራት እርዝማኔ 29 ወይም 30 ቀናት ይሆናል። የዓመቱ ጅማሮም በፀሐይ ይወሰናል" በማለት ያስረዳሉ።

ልማዳዊው የቻይናውያን የዘመን ቀመር በመላው ምሥራቅ እስያ በተለያዩ ሁኔታዎች ጥቅም ላይ ይውላል።
Lunar.jpg
Credit: Getty Images/d3sign
ፓን ዋንግ፤ በየዓመቱ የሉናር አዲስ ዓመት አንድም ጃኑዋሪ አለያም ፌብሪዋሪ ላይ እንደሚውል ሲገልጡ፤

"አዋዋሉ በጃኑዋሪ መጨረሻና በፌብሪዋሪ አጋማሽ ላይ ባሉት ጊዜያት ነው። በዚህ ዓመት የሚውለው ፌብሪዋሪ ላይ ነው" ብለዋል።

የፋኖስ ፌስቲቫል

የሉናር አዲስ ዓመት ክብረ በዓል በልማዳዊነቱ ከሉናር አዲስ ዓመት ዋዜማ በሉናር አዲስ ዓመት በገባ ኣሥራ አምስተኛው ቀን እስከሚከበረው ፋኖስ ፌስቲቫል ድረስ ለአሥራ አምስት ቀናት እንደሚዘልቅ ዶ/ር ካይ ጃንግ ሲናገሩ፤

በቻይና ዘመን አቆጣጠር የፋኖስ ፌስቲቫል ከአዲሱ ዓመት የወሩ አሥራ አምስተኛው ቀን ጋር ይገጣጠማል፤

"ይህም የፋኖስ ፌስቲቫል ተብሎ ይጠራል፤ ስለምን ቤተሰቦች ጥንታዊ ልማዶችን ተከትለው ለልጆቻቸው ትናንሽ ፋኖሶችን ይሠራሉ፤ ከበሮቻቸው ውጪ በርተው እንዲታዩ ያደርጋሉ"

"በዚያን ቀን ትልቅ ኩነት ይዘጋጅ እንደነበር በታሪክ እስከ ታንግ ስርወ መንግሥት ወደ ኋላ መጓዝ እንችላለን"ብለዋል።

"ለቅድመ አያቶች ከበሬታን መቸር"

ዶ/ር ክሬይግ ስሚዝ በሜልበርን ዩኒቨርሲቲ የእስያ መካነ ጥናት የትርጉም ጥናቶች (የቻይና ቋንቋ) ገዲብ መምህር ናቸው።

ታይዋንና ደቡብ ኮሪያ ውስጥ ለጥቂት ዓመታት የኖሩ ሲሆን በሁለቱም አገራት የሉናር አዲስ ዓመት ክብረ በዓላትን አስመልክቶ ትልቅ ትውስታዎች አሏቸው።

ዶ/ር ስሚዝ ደቡብ ኮሪያ ውስጥ የሉናር አዲስ ዓመት ዕለት ሌሎች ባሕሎችም የሚጋሩት ለቅድመ አያቶች ከበሬታን የመቸር ልማድ መኖሩን ሲናገሩ፤

"በአዲስ ዓመት ቀን ሁሉም ሰው በሕይወት ለሌሉ ቀደምት አባቶችና እናቶች ምግብና መጠጦችን ያቀርባሉ፤ ከበሬታቸውን ይቸራሉ" ብለዋል።
رقص شیر.jpg
رقص شیر Credit: Getty Images/Nigel Killeen

"ሺህ ዓመታት በምልሰት የሚጓዝ ታሪክ"

ዶ/ር ስሚዝ ከቻይና ሌላ የሉናር በዓል ክብረ በዓላት ከበሬታን አስመልክቶ ከሌሎች አገራትም የተዛነቁ ልምዶች መኖራቸውን ይናገራሉ።

ለአብነትም በሉናር አዲስ ዓመት ወቅት የሚቀርበውን ልማዳዊውን የአንበሳ ዳንስ ትዕይንት ይነቅሳሉ።

"የቀለም ሰዎች የላይን ዳንስ ልማድን ሲመለከቱ አሁን ምዕራብ ወይም ማዕከላዊ እስያ ብለን የምንጠራቸው አገራት ውስጥ ከዝነኛው የሐር መንገድ ጋር ተያይዘው መጥተው የምናውቃቸውን አያሌ ልማዶች፣ ሃይማኖቶች፣ ሙዚቃ፣ ስነ ጥበባት ከቻይና መምጣቸውን ሺህ ዓመታት በምልሰት ተጉዘው ነው" ብለዋል።
የተወሰኑት የእኒህ ልማድ መሠረቶች ከቻይና ውጪ የመሆን ሁኔታ ከፍ ያለ ሊሆን ይችላል። በቋንቋዊና ታሪካዊ ትንታኔዎች መሠረት አያሌ ሰዎች ከፐርዥያ ልማዶች ጋር ግንኙነት አላቸው።
2024 የድራጎን ዓመት ነው።

የቻይና ዞዲያክ ዓመት የሚነሳውና የሚያበቃው በሉናር አዲስ ዓመት ነው።

እያንዳንዱ ዓመት በየ12 ዓመት ዑደት በዞዲያክ እንሰሳ ተወክሎ ባሕርዩን ሳይለውጥ ራሱን ይደግማል።

ዓመታቱ የሚጠሩበት የዞዲያክ እንሰሳት በቅደም ተከተል አይጥ፣ በሬ፣ ነብር፣ ጥንቸል፣ ድራጎን፣ እባብ፣ ፈረስ፣ ፍየል፣ ዝንጀሮ፣ አውራ ዶር፣ ውሻና አሳማ ናቸው።




Share
Published 6 February 2024 9:13am
Updated 6 February 2024 9:24am
By Chiara Pazzano, Kassahun Seboqa Negewo
Source: SBS

Share this with family and friends