አድዋ ድሌ ተሽከረከረች!

*** በ ገለታው ዘለቀ

Community

A woman blows a trumpet as Ethiopians celebrate the victory at the Battle of Adwa on March 02, 2021 in Addis Ababa, Ethiopia. Source: Getty

ያምማል እያለ የከተተው 

ጉሮ ወሸባው አባተው

የጅግንነት የውኃ ልኬት 

የህብር ክንዳችን ጉልበት

የትብብራችን ብርታት

መልህቅ ያገር አንድነት 

 

አድዋ......

 

ማሳያ ልኬታችንን

የአብሮነት ቃል ኪዳን ውላችንን

የነፃነትን ዋጋ ክብራችንን

 

አድዋ ክብሬ ናት ኩራቴ 

ታሪኬ እምዬ ስስቴ

 

አያ ሆ ሆ ተሽከረከረች.....

 

አንቺ  እርግብ ሆይ ብረሪ

የአድዋ ተራሮችን ድል አብስሪ

የድል ዝማሬን ዘምሪ

ላለም ህዝቦች ሁሉ መስክሪ!

 

በቅኝ ግዛት ብትር ቆስለው

አንገታቸውን ቀልሰው

የሃዘን በርኖስ ደርበው

ተከፍተውና ቆዝመው

ጉልበታቸው መሬት ጠቅሶ

 ከንፈራቸው መሬት ልሶ

 ብሶት ሆዳኛቸውን አብሶ

የደም እምባ ሲያለቅሱ

ሃዘን ተጭኗቸው ሲተክዙ

እነሆ ከአፍሪካ ቀንድ ላይ

ከአድዋ ተራሮች ላይ 

የምስራች ድምፅ ተሰማ

ነጋልህ ጭቁን ቀናበልማ

መፅናናት ይሁን ለራማ

 

ያምማል እያለ የከተተው

ጉሮ ወሸባው አባተው

 

የቅኝ ግዛቱን ጉልበቱ ራደው

የግዛት ዘንጉ  በረደው

 

በምስራቅ አፍሪቃ ኮከቦች

በኢትዮጵያ ድንቅ ልጆች

 

እነሆ ......

 

አዲስ ምእራፍ ተከፈተ

የነፃነት ብርሃን አባተ

ያምማል እያለ የከተተው

ጉሮ  ወሸባው አባተው

 

አድዋ ድሌ.....

 

አያ ሆሆ ተሽከረከረች

ሞገሴ አድዋ ዛሬም ከበረች

አያ ሆ ሆ ተሽከረከረች

ዛሬም ኢትዮጵያ አንድ ናት አለች

 

አድዋ.....

 

እናንት የአድዋ ተራሮች

የአንድነታችን ህያው ምስክሮች

ብርሃናችሁ ዛሬም ይብራ 

ይፈንጥቅ የንጋቱ ጮራ

ግለጡ የተፃፈባችሁን 

አሳዩ ማተማችሁን

 

አያ ሆ ሆ ተሽከረከረች.....

 

ዘመኑ ሄደ ዘመኑ ጠባ

የአድዋ ፅዋ ከቤቴ ገባ

 

አያ ሆ ሆ ተሽከረከረች

የአድዋ ድሌ ዛሬም ከበረች

 

አያ ሆ ሆ ተሽከረከረች

ዛሬም ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ 'ያለች!

 

አያ ሆ ሆ ተሽከረከረች 

እኔ ከኢትዮጵያ ወይ ፍንክች አለች!

 

ድል ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነት!

      

 መጋቢት፣ 2013


Share
Published 28 February 2022 4:51pm

Share this with family and friends