ኤምባሲው በአውስትራሊያ፣ ኒውዝላንድና በአካባቢው አገሮች ነዋሪ ለሆኑ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ባስተላለፈው የድል በኣል መልዕክቱ፤
"የዛሬ 128 ዓመት አገራችን የተጋረጠባትን ወረራ ለመቀልበስ ጀኞች አባቶቻችንና እናቶቻችን ከሁሉም የአገራችን ክፍሎች በአንድነት በመዝመት አጥንታቸውን ከስክሰውና ደማቸውን አፍሠው ጠብቀው እንዳቆዩን ሁሉ አገራችንን አንድነቷና ሰላሟ ተጠብቆ ለትውልድ ለማስተላለፍ በጋራ መሥራት እንደሚጠበቅብን፤ ለዚህም የሁሉም ዜጎችና የኢትዮጵያ ተወላጆች ትብብር እንደሚጠበቅ ያምናል" ብሏል።
አክሎም "በቀጣናው አገራት ነዋሪ የሆናችሁ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ልዩነቶችን በሰከነ መልኩ በሰላማዊ መንገድ፣ በንግግርና በድርድር ለመፍታት ለሚደረጉ አገራዊ ትረቶች መሳካት የሚጠበቅባችሁን አስተዋፅዖ እንድታበረክቱ አገራዊ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን" ሲል አሳስቧል።
በአውስትራሊያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ "ተደራሽነቱን ይበልጥ ለማስፋትና አገልግሎቱንም ዜጎች በሚኖሩባቸው ከተሞች ሁሉ ተደራሽ ለማድረግ ከሁሉም አካላት ጋር በቅርበት ለምሥራት ዝግጁ መሆናችንን በድጋሚ እያረጋገጥን ለምትሰጡን አስተያየትና ድጋፍ ሁሉ እናመሰግናለን" በማለት መሰናዶውን አመላክቷል።