ቦታ የለም የሚለቀስበት
ቃል የለም የሚፅናኑበት
ብርታት የለም የሚታለፍበት
መጨረሻህ ሰዓት የሚታወቅበት!!
በብዙ ሰው መሀል ያለ ብቸኝነት
በሁካታ መሀል የዝምታህ ጩኸት
ሳንሰማው ያለፍነው ያ የነፍስህ ተረክ
እንግዳችን ሆነ ለሞት ሲንበረከክ።
ሸራህም ይወጠር ቀለምም ይቀየጥ
ይቻለው እንደሆን እኛን የማስመለጥ
ብሩሽህ ይዳሰው ዛሬን ትላንትህን
ያወጋችሁትን ስትይዘው ብቻህን።
እሳት መሳይ ቀለም ብሩሽህ ይተፋል
የነጣው ሸራህም ሊሳል ይጎመጃል
ሙዚቃ ነው ልብህ ጥበብ ነው መንፈስህ
በሳቅ በፈገግታ የሚያጨዋውትህ።
ጎዳና ነው ስዕልህ ናዝሬት አዲስ ‘አባ
የሚያመላልስ ሸራ ባለ ጀልባ
እጣን ነው ስዕልህ በጭስ የከበበ
ተመልካች የሚያውድ ለልብ የቀረበ።
ህይወትህ ቀለም ነው ሀምራዊ አረንጓዴ
ከራስ የተስማማ ያንተ ዓለም ጓዴ
ማሀላ ነው ስዕልህ የቀለመ አማልክት
ሰግደው የማረኩት ያገርህ ምልክት።
እና ታምዬ
ቋጭተህ ያልጨረስከው ትላንት የነደፍከው
ድምፅ ያውጣ ስዕልህ ላለም ይናገረው።