የባለ ቅኔ ቀን !!

ዓባይና ጣና መለያያ ድልድይ ስር የተፃፈ

Poetry Demeke

Journalist Demeke Kebede Source: Supplied

ዓባይ ድልድዩ ስር...

ዓባይ እያጓራ - እየተፎገላ

ደም መሳይ ገላውን - ወርሶ ከአፈር ገላ

ሽልምልም እያለ - ከጣና ሲነጠል - ከጣና ሲከላ

ቁጭ ብዬ እያየሁ

እኔ እጠይቃለሁ

ከሀሳብ አድማሳት

ሀሳብ አስሳለሁ

የባለቅኔ ቀን  - የባለቅኔ አገር - ወዴት ናት እላለሁ፤

 

ይህ ሽበታም ድልድይ...

በጫንቃው መኪና - እንደተሸከመ

በጉያው ዓባይን  - ሰርክ እንዳስተመመ

በቁር ሳይርድ ገላው - ሳይበድን አካሉ

የመጣን፣ የሄደን

እየተሸከመ - ሲያሳልፍ እያየሁ

በሸክሙ እደክማለሁ - በሸክሙ እዝላለሁ፤

 

እና እንዲህ እላለሁ

የልቡን እምቃት - እስትንፋሱን ሁላ - አልፎ ሂያጅ ለቀማው

እህ ባለ ጊዜ  - ላጣ የሚሰማው

ከእንጉርጉሮው ዜማ - ሀሳብ ለመቀመር

ከሸክሙ ቅኔ ውስጥ - ትንሳኤ ለማብሰር

ሀሳብ አወጣለሁ

ሃሳብ አወርዳለሁ

ሀሳብ አስሳለሁ

የባለቅኔ ቀን - የባለቅኔ አገር - ወዴት ናት እላለሁ፤

 

‹‹ዓባይ ሽልምልሙ

ጣና ስልምልሙ

ድልድዩ ሽልሙ

አንድም ሳይጣሉ

አንድም ሳይስማሙ

እሾህ ያበቅላሉ

ዋርካ እያወደሙ፤››

ይላሉ ወፎቹ

ከጣና ስርቻ - ከዓባይ በስተግርጌ - ዛፍ ላይ የሰፈሩት

የድልድዩን ቅኔ - በጣና ሙዚቃ - በዓባይ ሲቀምሩት፤

 

ይህን እያየሁ

ሀሳብ እጥላለሁ

ሀሳብ እሰቅላለሁ

ከሀሳብ አድማሳት

ሀሳብ አስሳለሁ

የባለቅኔ ቀን - የባለቅኔ አገር - ወዴት ናት እላለሁ፤

እላለሁ፤ እላለሁ

በቁጭት ሰበዜ

የህልሜን አክርማ

ስፌት እሰፋለሁ፤

 

ስፌቱ ጣናዬ

ዓባይ አክርማዬ

ድልድዩ ሰበዜ

የወፎቹ ዜማ - ወስፌ ነው መስፊያዬ - ስል እሞግታለሁ

በሀሳቤ ውጥን - ህዝብ እሰብዛለሁ - አገር እሰፋለሁ

ከመሸችው ጀንበር

ግራምጣ ሰግስጌ - ህዝብ አተልቃለሁ - አገር አልቃለሁ፤

 

ይህንን ከፍታ - ደግሜ አደምጣለሁ

ባሳብ ሰረገላ - እመነጠቃለሁ

ከዝምታ ስፌት - ህልም አስቀምጣለሁ፤

 

ከወፍ የተቀዳ - ከዓባይ የተሰማ - ከሀይቅ የተገኜ - ሙዚቃ እየሰማሁ ድልድይ ስር ሆኜ - ዋርካ ተከልዬ - የባለቅኔ ህልም ልፈታ እጥራለሁ፤

 

አሁንም ያው አለሁ

ሀሳብ አወጣለሁ

ሀሳብ አወርዳለሁ

ከሀሳብ አድማሳት - ሀሳብ አስሳለሁ

ህልም እሚፈታባት

የባለቅኔ ቀን

የባለቅኔ አገር - ወዴት ናት እላለሁ፤

 

ታዲያ ሁላችሁም - በድንገት መጥታችሁ

ተነስ ካለህበት - ቤት ግባ ብላችሁ

ተውኝ አትቀስቅሱኝ

ካሳቤ አትመልሱኝ

ህልሜን አገሬ አውቃው - በአገሬ እስኪሰማ - በአገሬ እስኪነገር ተውኝ ሳስስ ልኑር - የባለቅኔ ቀን - የባለቅኔ አገር።

 

2005 ዓ ም

 


Share
Published 14 August 2020 10:26am
By Demeke Kebede

Share this with family and friends