ሞት ማስደንገጥ ሲያቅተው

ሥነ ግጥም

Kebedech's poem Death

Kebedech Tekleab Source: Courtesy of KTA

ሞት ማስደንገጥ ሲያቅተው

ያን ጊዜ ነው

ምን መሆኔን የማላውቀው።

ነፍስ ከስጋ ስትለይ

ተመልሳ ላትከተት

የእንቁላል ዘመኑን አልፎ

ሰብሮ እንደወጣ ነፍሳት

እንኳን በግፍ ተሰርቃ

እንደሷ ሕይወት ባዘለ

በመሰሏ እጅ ተነጥቃ

በእንቅልፍ ዓለም

እንኳን ብትቀር

ጀንበር ሲጠባ ባታይ

ለወትሮው

የቋሚው የውስጥ ለቅሶ

የኗሪው የውስጥ ብካይ

በቋሚው ውስጥ ነፍስ እንዳለ

የሚያሳይ ምልክት ነበር

ሰውን እንደ ሰው ሲያከብር

ምክንያት ለማዳን እንጂ

ጥብቅናው ለሞት ከሆነ

ልቤ

ህልፈት ካደነደነው

ነፍስ ሲጠፋ ካላዘነ

ማልቀስ ያለብኝ ለኔ ነው

በውስጤ ሕይወት ለሞተው

የፍትህ ዘር ለማልዘራው

አመፅ በመላ ለማልፈታው

ብሶት በሚዛን ለማልዳኘው

የሰላም ምርት ለማላጭደው

የሰው ሞት ካደነደነኝ

ማልቀስ ያለብኝ ለኔ ነው።

ከበደች ተክለአብ

እንደ አውሮጳ አቆጣጠር ጁላይ 2020

*ይህ ግጥም ቀደም ሲል በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ለሕትመት በቅቷል።


Share
Published 3 August 2020 12:21pm

Share this with family and friends