እንደመግቢያ
ግርማ አውግቸው ከዚህ በፊት በርካታ የምርምር ጽሁፎችን በግሉም ሆነ ከሌሎች ተመራማሪዎች ጋር ለስነልሳኑ ማህበረሰብ አበርክቷል። ከዚህም በተጨማሪ “The origion of Amharic” የሚለው መጽሃፉ በአማርኛ ቋንቋ አመጣጥ ዙሪያ የቀረቡ የተለያዩ መላምቶችን በተጨባጭ ማስረጃ በመሞገት ተጨማሪ የምርምር ስራዎች ይሰሩ ዘንድ አመላክቷል።
በሌላም በኩል ቋንቋ እና ነገድ በኢትዮጵያ፡ የኢትጵያ ህዝብ ማንነትና ቅድመ ታሪክ በተሰኘው መጽሀፉ የታሪካዊ እና የአይነታዊ የስነልሳን ጥናቶችን መነሻ በማድረግ በአጥጋቢ እና በተጨባጭ መረጃዎች ላይ ተመርኩዘን ወደ ማጠቃለያ መድረስ ካልቻልን የጥናት ውጤቶቻችን አከራካሪ እና አሻሚ መሆናቸው እንደማይቀር አመላክቷል። እንደ ማሳያም የሴማዊ ቋንቋ ተናጋሪ ቤተሰቦች ከቀይ ባህር ማዶ ተሻግረው ለመምጣታቸው በሰሜን ኢትዮጵያ አምሳያ ቃላቶች ከቦታዎቹ ስያሜ ጋር መኖራቸው መሰረታዊ መረጃ ተደርጎ ቢወሰድም በታሪክም ሆነ በስነልሳን ተጨባጭ ማስረጃዎች አስደግፎ ለመሞገት አስቸጋሪ እንደሆነ አስፍሯል። ይህ ደግሞ ከዚህ በፊት የተጠኑ ጥናቶች እንደገና በስነልሳን ምሁራን ቢፈተሹ ውጤቱ ሊቀየር እንደሚችል ከመጽሀፉ አጠቃላይ ይዘት መረዳት ይቻላል።
የመጽሐፉአጠቃላይይዘትፍተሻ
ከላይ ከተጠቀሱት ስራዎች በተጨማሪ ደራሲው ተከታታይነት ያላቸው ነገርግን በራሳቸው ሙሉ የሆኑ አራት መጽሃፎችን ለማሳተም ራዕይ ሰንቆ ሁለቱን እውን ያደረገ ሲሆን የኩሻዊ ቋንቋዎችን እና ተናጋሪዎቻቸውን እንዲሁም የኢትዮ- ሴማዊ ቋንቋዎችን እና የህዝቦችን ታሪክ ወደፊት ለማቅረብ ጠንክሮ እየሰራ ይገኛል። ይህ ሁሉ ሲሆን የደራሲው ዋና አላማ የተለያዩ ምሁራን በስራዎቻቸው ውጤት የሚወዛገቡባቸውን የኢትዮጵያ ቋንቋዎች በአይነትና በዘር ምደባ ዙሪያ ሳይንሳዊ የሆነ የስነልሳን ጥናት ላይ ተመስርቶ በተጨባጭ ማስረጃዎች በማስደገፍ ትንታኔዎችን ማቅረብ ነው።
ቋንቋ እና ነገድ በኢትዮጵያ ቅጽ ሁለት ውስጥ ያሉት ጉዳዮች በአምስት ምዕራፎች የተከፋፈሉ ናቸው። በውስጡም የኦሞአዊ፣ የአባይ ሰሃራዊ እና ምድብ ያለየላቸው ቋንቋዎች እና ህዝቦቻቸውን በዋናነት የዳሰሰ ሲሆን በኢትዮጵያና በኤርትራ ላይ ትኩረት አድርጓል።
በመጽሃፉ የመጀመሪያ ምዕራፍ ቋንቋ እና ህብረተሰብን እንደ ርዕሰ ጉዳይ በማንሳት በቋንቋዎች መካከል ያለውን የውህደት እና የማንነት መቀየርን ጽንሰ ሀሳብ ወደፊት ስለሚተነትናቸው ቋንቋዎች እንደመንደርደሪያ ይሆኑት ዘንድ አጠር ያለ ማብራሪያ ሰጥቷል፤ እንደማስረጃም የአርጎባ ብሄረሰብን፣ ኦሞአዊ እና የናይል ሰሃራዊ ቋንቋ ተናጋሪዎችን ከጠቀሰ በኋላ ውርርሱም በእነዚህ ቋንቋዎች እንደማያበቃ አስፍሯል። የቋንቋውንም ሆነ የህዝቡን ቅድመ ታሪክ በይበልጥ ለመረዳት በሚደረግ ጥረት የታሪካዊውም ሆነ የአይነታዊው ስነልሳን ጥናት አቅም ውስንነት በቋንቋውና በህብረተሰቡ ውስጥ ያለውን መስተጋብር በውል ለመረዳት አዳጋች መሆኑን አመላክቷል።
በሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ ከዚህ በፊት በልዕለ-አፍሮኤዢያዊ ስር ኦሞአዊ ቋንቋዎች ይወርዳሉ ወይስ ለብቻቸው ተነጥለው ወይም ራሳቸውን ችለው ይቀመጣሉ ወይም እራሱስ እንደ አንድ ቤተሰብ ሊታይ የሚችል ነው በሚለው ጉዳይ የእነ ፍሌሚንግ (1969፣ 1973፣ 1974፣ 1976 ሀ እና ሐ)፣ ቤንደር (1971፣ 1975)፣ ሳዝ (1972)፣ ኒውማን (1980)፣ ታይል (2006)፣ ዞበርሲኪ (1989)፣ ዲያክኖፍ (1996) የሚያነሷቸውን ሀሳቦች እያመጣ የራሱን ተጨባጭ ማስረጃዎች በማስቀመጥ ቋንቋውን ከህዝቦች ጋር እያስተሳሰረ ነገሮችን ከተለያዩ አቅጣጫዎች በመመልከት ይሞግታል። በሶስት ቡድኖች የተነሳውንም አጠያያቂ ጉዳይ ከክፍፍሉ፣ ከጥንታዊነቱ፣ እና ከባህሉ ጋር አቆራኝቶ የተለያዩ ማብራሪያዎችን ከነማስረጃዎቹ አቅርቧል።
በኦሞአዊ ቋንቋዎች ቁጥር ጉዳይ የተለያዩ ምሁራን የሚያሰፍሩት ሰፊ የሆነ የአሀዝ ልዩነት መኖሩን አስረድቷል። እንደ ደራሲው ገለጻ፡- የዚህ ምክንያት ስለ ኦሞአዊ የንግግር አይነቶች የዝምድና ደረጃ እና እርስ በርስ ግንኙነት ያለን ግንዛቤ አጥጋቢ ደረጃ ላይ የደረሰ አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን ውስብስብነት ያለው መሆኑን በመጽሃፉ ላይ ያስቃኘናል።
በሌላም በኩል በቋንቋ እና በዘዬ መካከል ያለው ግልጽ ልዩነት ወይም ድንበሩ ባለመታዎቁ እና በዘዬዎች ቅጥልጥሎሽ ምክንያት በኦሞአዊ ቋንቋዎች በተለይም በኦሜቶ የንግግር አይነቶች መሀከል ተመሳሳይ ሁኔታ መኖር ሌላው የልዩነቱ ማሳያ ነው። በዚህም ምክንያት በተለያዩ ምሁራን ቋንቋ ናቸው ተብለው የቀረቡት በጣም የሚቀራረቡ የዘዬ ዝምድና ያላቸው መሆኑን ደራሲው ማስረጃ እያጣቀሰ ያስረዳል።
በዚህ መጽሀፍ ናይል ሰሃራዊ ከምስራቅ ኩሻዊ ቋንቋዎች ጋር የተወራረሰ በመሆኑ በኦሞአዊ ንዑሳን ቤተሰቦች መካከል ያለውን ግንኙነት በግልጽ ለማውጣት አስቸጋሪ እና ውስብስብ መሆኑ ተብራርቷል።
ግርማ አውግቸው የኦሞ ህዝቦች ባህልና ቅድመ ታሪክ ጥንታዊነት ያለው በመሆኑ በንዑሳን ክፍሎች መሀከል ያለው ልዩነት መስፋቱን ከተለያዩ ማስረጃዎች ጋር እያገናኘ እንደምክንያትነት ያስቀምጣል። የኦሞአዊ ህዝብም ከሌላው ወረሳቸው የማይባሉ የእርሻ ተግባራት እንዳሉት ይገልጽና ምናልባትም እንሰትን ለምግብነት በማዋል የመጀመሪያዎቹ ሳይሆኑ እንደማይቀር አስፍሯል። ከዚህም በተጨማሪ በውስጡ ያሉትን ቋንቋዎች በስድስት ቡድኖች በመመደብ እና በእነሱም ውስጥ ያሉትንም ቋንቋዎች በመፈተሸ ዘርዘር ያሉ ማብራሪያዎችን ደራሲው ለመስጠት ሞክሯል።
ምዕራፍ ሶስት ደግሞ የናይል ሰሃራዊ የቋንቋ ቤተሰብን በውስጡ አካቶ የያዘ ሲሆን እንደ ቋንቋ የዘር ቤተሰብነት የሚያስወስዱት ባህሪያትን፣ የቋንቋዎችን የእርስበርስ ዝምድና እና ስርጭት የተቃኘበት ክፍል ነው።
ደራሲው የአባይ ሰሃራዊን እንደዘር የቋንቋ ቤተሰቦች ለመውሰድ ያለው መረጃ ልል እንደሆነ ከጠቀሰ በኋላ በውስጣዊ ክፍሉም ዙሪያ እና ግሪንበርግ (1963)፣ ዌስተርንማን (1912)፣ ቤንደር (1975፣ 2000 ለ)፣ ብለንች (2010)፣ ዲመንደል (2011) እና ስታሮስቷን (2016) በአብዛኛው ስምምነት ላይ እንዳልደረሱ ያደረጉትን ክፍፍል እንደማስረጃ በማሳየት አመላክቷል።
ናይል ሰሃራዊ ቋንቋ በርካታ የአፍሪካ ሀገራትን የሚሸፍን እና በኢትዮጵያም በአብዛኛው በምዕራቡ ክፍል እንደሚገኝ አስፍሯል። ነገርግን እንደ ቋንቋ የዘር ቤተሰብነት ለመውሰድ አስቸጋሪ መሆኑ፣ በዚህ ውስጥ ያሉት ቋንቋዎች የሚጋሯቸው ባህሪያት ማግኘት ከባድ መሆኑ፣ ባህሪያቱም ቢገኙ እንኳ የዘር ስለመሆናቸው ለማረጋገጥ አሳማኝ ማስረጃ አለመገኘቱ ወዘተ. አከራካሪ ጉዳዮች እንደሆኑ አመላክቷል። ከዚህም በተጨማሪ በሌሎች ሶስት ታላላቅ ቤተሰቦች ፡- አፍሮ- ኤሽያዊ፣ ኒጀር፣ ኮንጎ፣ እና ኮኻሽያን የማይመደቡትን ቋንቋዎች ሰብስቦ የያዘ ከመሆን የዘለለ አይደለም በሚል ወቀሳ እንደሚቀርብበትም አክሎ ጠቅሷል።
በኢትዮጵያ የሚገኙ የናይል ሰሃራዊ ቋንቋዎች አሃዝ በተለያዩ ምሁራን የተለያየ ነው። ለምሳሌ ሀድሰን (2017) አስራ ሰባት ናቸው ሲል፣ ዲመንተል (2011) ደግሞ 22 እንደሚያደርሳቸው እና ጫቡ ቋንቋን ደግሞ ምድብ ያልተገኘለት ቋንቋ አድርገው እንዳሰፈሩት ይገልጽና በሁለቱም ስራዎች ያልተጠቀሱ እና ሰፊ ጥናት የሚያስፈልጋቸው ሌሎችን ጨምሮ ደራሲው ቁጥራቸውን 24 እንደሚደርስ መረጃ ይሰጣል። ከእነዚህ ውስጥም ከናይል ሰሃራዊ ቋንቋዎች ዝምድና የሌላቸው በኤርትራ የሚነገሩት ኩናማ እና ናራ እንደሚገኙ በመጥቀስ ስለቋንቋዎችም ሁኔታ ከሌሎች ዋቢዎች ጋር እያጣቀሰ ያስረዳል።
በምዕራፍ አራት ላይ ደግሞ እስከ አሁን የተለያዩ ምሁራንን እያወዛገቡ ያሉ እና ከሌሎች ዘር ቡድኖች ጋር የሚያስተሳስር አጥጋቢ መረጃ ያልተገኘላቸው ሁለት ቋንቋዎችን ያነሳል። እነሱም ስያሜያቸው ወጥ ያልሁኑት ሻቡ/ጫቡ እና ኦንጎታ/ ቢራይሌ ቋንቋዎች ሲሆኑ ስለ ዘር ምድባቸውም ሆነ ስለ ሰዋስዋዊ መዋቅራቸው የተለያዩ የምርምር ስራዎችን እያጣቀሰ በሰፊው ያብራራል። ከዚሁ ጋር አያይዞም የምልክት ቋንቋን እንደ ቋንቋ ትምህርትነት መሰጠት የተጀመረበትን ታሪካዊ ዳራ በመዘርዘር የዘዬ ልዩነትም በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች እንደሚስተዋል እና የመደበኛነት ጥያቄም የሚነሳበት መሆኑን ከጠቀሰ በኋላ ጉዳዩ ሰፋ ያለ ጥናት እንደሚያስፈልገው ያትታል።
በመጨረሻም በመጽሃፉ ውስጥ በጣም ጠቃሚ የሆኑ አባሪዎች፡- የዓጼ ይስሃቅ መወድስ፣ የአፍሮኤሽያዊ፣ የኢትዮሴማዊ፣ የኦሞአዊ፣ የኩሻዊ እና የጠፉ ቋንቋዎች እንዲሁም የአማርኛ ሆሄያት ምርጫ፣ የመረጃ አጠቃቀስ፣ የእንግሊዝኛ ሙያዊ ቃላት እና የእንግልዝኛ/ ላቲን ፊደል አጠቃቀም፣ የመረጃ አጠቃቀስ፣ ሙዳዬ ቃላት፣ ዋቢ ጽሁፎች እና ቅሱም (ኢንዴክስ) ተካተውበታል።
በአጠቃላይ ደራሲው ከጥንት የመረጃ ምንጮች አዳዲሶችን እያስተሳሰረ ምሳሌዎችን እና ተጨባጭ መረጃዎችን እያመጣ መረጃቸው የሚያጠራጥሩትን ስራዎች ተጨማሪ ምርምር እንዲሰራባቸው እየጠቆመ የሚያልፍ ከመሆኑም በላይ በኦሞአዊ፣ በናይል ሰሃራዊ እና ምድብ ባልተገኘላቸው ቋንቋዎች ላይ የተለያዩ የጥናታዊ ጽሁፎችን ለሚያቀርቡም ሆነ ለቅድመ እና ለድህረ ምረቃ ተማሪዎች እንደማጣቀሻነት የሚያገለግል በመሆኑ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። ደራሲው “የኩሻዊ ቋንቋዎች እና ተናጋሪዎቻቸው” የሚለውን ሶስተኛውን መጽሃፍ በቅርቡ ለንባብ እንደሚያበቃ ምኞቴ ነው።
መንግስቱ ታደሰ ሞላ
ደብረብርሃን ዪኒቨርሲቲ፣ ደብረብርሃን፣ ኢትዮጵያ