ረዘነ ሃብተ። 2019 እ.አ.አ.። ደም የተከፈለበት ባርነት፤ የኤርትራ አብዮት ህልሞችና ውድቀት። ትሪንተን፤ ዘ ሬድ ሲ ፕረስ። 314 ገፆች፣ 5.5X8.5”
“በግብፅ ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት የኤርትራ ነጻ አውጪ ድርጅት (ጀብሃ) እ/ኤ/አ በ1960 ዓ.ም ከተመሰረተ በኋላ በ1961 ዓ.ም የትጥቅ ትግል ተጀመረ። ሃይማኖታዊ እና ዓረባዊ አጀንዳ ለማስፈጸም በዓረብ መንግስታት ቀጥተኛ ድጋፍ የተመሰረተው [የ]ጀብሃ መሪ የነበረው ኢድሪስ መሐመድ አደም በተመሳሳይ ሁኔታ የፌዴሬሽኑ ከፍተኛ አመራር አባል ነበር” (ገፅ 12)።
1. መግቢያ
ደም የተከፈለበት ባርነት የሚለው መፅሀፍ በኢትዮጵያ እንደታተመ ባውቅም እጄ የገባው አሜሪካ በዘ ሬድ ሲ ፕረስ ከታተመ በኋላ ነው። መፅሀፉን ለማንበብ የጓጓሁት የመፅሀፉን ማውጫ፣ ማጠቃለያ ወይም ዝርዝር ማስታወቂያ አይቼ አልነበረም። በምን አጋጣሚ እና ከየት እንደሆነ አሁን ትዝ ባይለኝም ደም የተከፈለበት ባርነት በሚል ርዕስ መፅሀፍ እንደታተመ ሰማሁ። ርዕሱ ሳቢ ብቻ ሳይሆን ከባድ ድማዳሜም ነው። የእዚህ አይነት ርዕስ ለማውጣት/ለመስጠት አስተዋይነት ብቻ በቂ አይደለም። አስተማማኝ መረጃ መኖርንም ይጠይቃል። ምንም ሳይንዛዛ ርዕሱ በራሱ የመፅሀፉ ጭብጥን የሚያንፀባርቅ በመሆኑ፣ ዝርዝሩ ምንድነው፣ ደራሲው ይህን ለማለት ያበቃው ምን ምክንያት ይዞ ነው የሚለውን ለማወቅ ጓጓሁ።
ደም የተከፈለበት ባርነት ስለኤርትራው የ30 ዓመት ጦርነትና ውጤቱ የሚተርክ ነው፤ “የመጽሃፉ ዋንኛ ሃሳብ እና መሰረታዊ ዓላማ እርስ በእርሱ የሚጋጨውን የኤርትራ አብዮት ፖለቲካዊ ራዕይ፣ ያለፈበት ሂደት እና ያጋጠመውን ውድቀት ከተጠና ተጨባጭ እውነታ በመነሳት ፖለቲካዊ ትንታኔ ለማቅረብ ነው” (ገፅ 9)። ኤርትራ ከኢትዮጵያ በኃይል የተለየችበትን የነፃነት ባዩ ወገን “በደም የተገኘ ነፃነት” ሲለው፣ ይህን የማይቀበለው ልዩነትን የሚጠየፈው አብዛኛው ወገን ደግሞ “ለመገንጠል የተደረገ አላስፈላጊ መስዋእትነት” ይለዋል።
ደራሲው ግን ከዚህም ያልፋል። እንደደራሲው እይታ የ30 ዓመቱ ትግልና የፈሰሰው ደም ለባርነት የተደረገ መስዋዕትነት ነው። ይህ የደራሲው እይታ ለመፅሀፉ ትኩረት እንዲሰጠው የሚጋብዝ ነው። ይህን የሚለው ደራሲ ከሌላው ወገን ተሰልፎ ከሻዕቢያና ከጀብሀ ጋር ሲዋጋ የነበረ ሆኖ አይደለም። ደራሲው እራሱ በዚሁ በኤርትራው ትግል ቀጥተኛ ተሳታፊ የነበረ ነው። ለዚህም ነው ይህን መፅሀፍ እንደተራ ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ድርሰት በቀላሉ ወደጎን የማናደርገው።
2. የመፅሀፉ አደረጃጀትና አቀራረብ
ደራሲው ከላይ የጠቀስንውን የመፅሀፉን አላማ ያቀረበው በመጀመረያው አንቀፅ በመግቢያው ላይ ነው። ደራሲው ከዚህ በማስከተል በመግቢያው ያቀረበው ከመፅሀፉ ምን እንደምንጠብቅ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው። ደራሲው የአንባቢን ግዜ በከንቱ አያባክንም። ከጥሩ ድርሰቶች እንደሚጠበቀው ወደዋናው ቁም ነገር የገባው ምንም ጊዜ ሳይወሰድ ነው። የመፅሀፉን አካሄድና ጭብጥ ለመረዳት መግቢያውን ብቻ ማንበብ በቂ ነው። የዚህ አይነቱ አፃፃፍን ለመካን በሳል እውቀትና ሰፊ የፅህፈት ልምድን ይጠይቃል። እያንዳንዱ በመግቢያው የቀረበው አረፍተነገርና አንቀፅ ተስማማንበትም አልተስማማንበትም፣ ምንም ሳይሸፋፈን ደራሲው እውነት ነው የሚለውን ታሪክ ያቀረበበት ነው።
ዝርዝሩን ወደጎን አድርገን ይህን የደራሲውን አካሄድ ከመነሻው የተወሰኑ ነጥቦችን እንጥቀስ፤
“ይህ የሰሜኑ የኢትዮጵያ ግዛት በኢጣሊያ የቅኝ ግዛት ስር ከመውደቁ በፊት ኤርትራ የሚባል ሃገርም ሆነ ኤርትራዊ ማንነት እንዳልነበር ይታወቃል። በኢጣሊያ ኤርትራ የሚል ስያሜ የተሰጠው መሬትና ኤርትራዊ የሚል አዲስ ማንነት ያጠለቀው ህዝብ የኢትዮጵያ አካል የነበረ ነው። በ50 አመት የኢጣሊያ የቅኝ ግዛት ዘመን በሺዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያን ከአድዋው ጦርነት በፊትም ሆነ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ በመጓዝ ከወንድሞቻቸው ጎን ተሰልፈው ጸረ የቅኝ ግዛት ተጋድሎ ማካሄዳቸው በታሪክ ተመዝግቧል። በኢጣሊያ ቅኝ ግዛት ዘመን ኤርትራዊ ማንነትም ሆነ ኤርትራ የሚባል ሀገር አልነበረም” (ገፅ 9)።
መግቢያው የመፅሀፉን ቁምነገር ጨምቆ የያዘ ነው ብለናልና፣ ቀጣይ ምዕራፎችን ማንበብ የደራሲውን መረጃዎች እና ዝርዝር ነጥቦች ለመመልከት ነው።
3. የህብረተሰብ ግንኙነት
ከመግቢያው በማስከተል ያለው የመጀመሪያው ምዕራፍ ስለኤርትራ ህዝብ የትመጣና ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ያለውን የቋንቋ እና የነገድ ትስስር የሚተነትን ነው። ደራሲው በዚህ ምእራፍ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ያለው ህዝብ በቋንቋ እና ነገድ መተሳሰሩ ብቻ ሳይሆን፣ በቅርብ ግዜም የአንድ ነገድ ህዝብ የሌላውን ቋንቋ እየወሰደ የሌላ ነገድ አባል ሆኖ እንደሚገኝ በርካታ ምሳሌዎችን እያመጣ ይጠቅሳል።
ይህን አስመልክቶ ከመፅሀፉ ሰፋ አድርገን እንጥቀስ፤
“አከለጉዛይ፣ ሐማሴን ሰራየ በሚል ስያሜ የሚታወቀው ህዝብ በተለያዩ ዘመናት ከተለያዩ የጐንደር /ቤገምድር/፣ ትግራይ፣ ጐጃምና ሸዋ አካባቢዎች ፈልሶ የመጣ ህዝብ ነው። ለምሳሌ ያህል የሐማሴን ሕዝብ ከቤጌምድር ደንቢያ ምናብ ከሚባል የዘር ግንድ የሚመዘዝ የሜሮኒ ጐሳ ከደንቢያ ወደ ሐማሴን በመምጣት የተዋለደ ህዝብ እንደ ሆነ በሰፊው ይታመናል። በአክሱምና በዛጉዌ ዘመነ መንግስት ከትግራይ፣ ከቋራ፣ ከደምቢያ፣ ከወገራ፣ ከላስታ፣ ከበለሳ እና ከጐጃም እንደሁም በዓፄ ዓምደጽዮን ዘመነ መንግስት ከሸዋ ሳይቀር ዳር ድንበርን ለማስከበር የዘመቱ እና በሰራየ፣ በሐማሴን እና በአከለጉዛይ የሰፈሩ በሺዎች የሚቆጠሩ የሰራዊት አባላት እዚያው ተዋልደውና ተባዝተው መቅረታቸው ይታወቃል። በዓፄ ዓምደጽዮን ዘመነ መንግስት ከሸዋ ሳይቀር ዳር ድንበርን ለማስከበር የዘመቱ እና በሰራየ፣ በሐማሴን እና በአከለጉዛይ የሰፈሩ በሺዎች የሚቆጠሩ የሰራዊት አባላት እዚያው ተዋልደውና ተባዝተው መቅረታቸው ይታወቃል።
“በዓዲ ሞንጎንቲ በሰራየ በለጎጭዋ፣ በከበሳ ጭዋ፣ ካር ነሸም፣ ሸውዓተ ዓንሰባ እና ሸማንጉስ ታሕታይ እንዲሁም በአከለጉዘይ በሎጎ ሳርዳ የሚኖሩት ዜጐች የዘር ግንዳቸው በአፄ ፋሲል ዘመን ከኢትዮጵያ ከመሃል አገር ከዘመቱ የሰራዊት አባላት የሚመዘዝ ነው። በ13ኛው ክፍለ ዘመን የዛጉዌ ስርወ መንግስት ከፈረሰ በኋላ የዓፄ ይኩኖአምላክ ወረራን በመፍራት ከላስታና ዋግ ሸሽተው በከረን እና አካባቢው ሰፍረው የቀሩት ብሌን /አገው/ መሆናቸው በታሪክ የተረጋገጠ ነው። ከእነዚሁ ውስጥ ወደ ሰራየ ሄደው እዚያ ከሚኖረው ህዝብ ተዋህደው የተዋለዱ ይገኙበታል። በአከለጉዛይ የሚገኙ የሮብራ እና እገላ ሓፂን ተወላጆች በዘመነ ዛጉዌ ከዓፄ ይትባረክ ወንድ ልጅ ጋር አብረው የመጡ ናቸው። በደቂ ገብራይ፣ ዓዲ ማቆም፣ እገላ ሓምስ እና አግነ የሚኖሩትም በዓፄ ዘርአያዕቆብና በዓፄ ዓምደ ጽዮን ዘመነ መንግስት በተፈጠረው የሃይማኖት ግጭት እንዲሁም በዓፄ ሰርጸ ድንግል ዘመን በነገደ ፈላሻዎች /ቤተ እስራኤል/ ላይ በደረሰው ጥቃት ምክንያት ሸሽተው የመጡ ናቸው። በዚያን ዘመን በመሃል አገር ይፈጠሩ በነበሩ ግጭቶች ሰበብ ወደ ባሕረ ነጋሽ /መረብ ምላሽ/ በመጓዝ የሰፈሩ ኢትዮጵያዊያን ቁጥር ብዙ ነው(ገፅ 24-25)”
ደራሲው እዚህ እና ሌሎች ጥቂት የማይባሉ ቦታዎች ላነሳቸው ነጥቦች የመረጃ ምንጮቹን አይጠቅስም። ከጠቀሰም የተሟላ መረጃ ብዙውን ግዜ ይጎለዋል። ሆኖም፣ የኢትዮጵያና እና የኤርትራ ህዝብ በነገድ እና በቋንቋ መተሳሰሩ በህብረተሰቡ ዘንድ የሚታወቅ ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ጥናቶችም ከቀደምት ግዜ ጀምሮ ሲሉት የነበረ በመሆኑ አዲስ ነገር አይደለም (ለምሳሌ ትሪሚንግሀም 1952/1965ን፣ ኡለንዶርፍ 1960ን እና ሌቪን 1974ን ይመልከቱ)። ከነገድ እና ከቋንቋ ዝምድናው በተጨማሪ ደራሲው ያነሳው የህብረተሰብ ከአንድ ቦታ ሄዶ የሌላው ጎሳ አባል መሆን፣ በመላው አለማችን የነበረ ታሪክ ነው። በኢትዮጵያ/ኤርትራ ደግሞ በስፋት የነበረ ነው። ለምሳሌ፣ ደራሲው ከጠቀሳቸው በተጨማሪ ሌሎችን ብንጨምር፤ በአፋር ሀውሳ የሚባሉ በመስኖ እርሻ የሚተዳደሩ ጎሳዎች አርጎባዎች እንደነበሩ ይገልፃሉ።
ዛሬ ጥንት የግዕዝና ጋፋት ተናጋሪ የነበሩ አሁን የጎሳ መለዮ ሳይኖራቸው በሌላው ተውጠው የቀሩ ናቸው (ለተጨማሪ መረጃ ግርማ 2018ን እና በእዚያ የተጠቀሱ ስራዎችን ይመልከቱ)። ከቡድን ወርደን በግለሰብ ደረጃም ብንሄድ ትስስሩ ከዚያ የበለጠ ሆኖ እናገኘዋለን። ዛሬ በእያንዳንዱ ቤት ማለት ይቻላል ያለው መዋሀድ እጅግ ሰፊ እንደሆነ ማንም ያጣዋል ማለት አይቻልም። ደራሲው ይህን የህብረተሰቡን ተጋምዶ ያመጣው ከታሪክም ባለፈ የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝብ አንድ ነው የሚለውን ሀቅ ለማሳየት ነው።
የዚህ ነጥብ እርባና የሚታየው ለኤርትራውና ዛሬም እንደአሸን በኢትዮጵያ ለፈሉት የጎጥ ፓርቲዎች መሰረት “ልዩ ነን” የሚለው የፖለቲካ ፍልስፍና በመሆኑ ይህንኑ ለመሞገት ነው። ከዚህ የዘለለ የፖለቲካ አስተሳሰብ ልዩነት ቢሆን ኖሮማ ስለህበረተሰቡ የአንድነት ታሪክና ዝምድና ማውራቱ ባላስፈለገ ነበር።በአለማችን ከኢትዮጵያ/ኤርትራ በላይ አንድ የሆኑ ህዝቦች በፖለቲካ ልዩነት ሲናቆሩ ኖረዋል፤ አሁንም የሚናቆሩ አሉ። አንዳንዶቹም ከኢትዮጵያው/ኤርትራው በከፋ፣ ለምሳሌ ሶሪያን ይመለከቷል፣ የቋንቋም ሆነ የነገድ ልዩነት ሳይኖርባቸው እርስ በርስ ሲጠፋፉ እና ህዝባቸውን ለችግርና ለሞት ሲዳርጉ ይስተዋላል።
የኢትዮ-ኤርትራው ግን ከአብዛኛው አለማችን የተለየ ሆኖ ይገኛል። የሌለ የማንነትና የታሪክ ልዩነት እንዳለ በማስመሰል የሀሰት ትርክት ፈጥሮ የፖለቲካ ትግል መነሻ እና መድረሻ ማድረግ ነው። ደራሲው የህብረተሰቡን የነገድ፣ የቋንቋ እና የታሪክ ትስስር ካነሳ በኋላ የሄደው ይህንን የሌለ ልዩነት የፈጠረው ዋናው ምክንያት ምን እንደሆነ፣ የፈጠራ ልዩነቱን የትግል መሳሪያ/አጀንዳ አድርገው በኤርትራው የሰላሳ ዓመቱ ትግል የተሳተፉት የፖለቲካ ፓርቲዎች አመሰራረትና አነሳስ ወደ መርመሩ ነው።
ኤርትራ በጣልያን አስተዳደር ስር በነበረችበት ወቅት ጣልያን በምታስተዳድረው ህዝብና በተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ መሀከል የማንነት ልዩነት ለመፍጠር ምን ያህል እንደተጓዘች ደራሲው በለተያዩ ሰነዶች አስደግፎ አቅርቧል። ይህ በእርግጥ የኤርትራን ጉዳይ ለሚከታተል ለማንኛውም ሰው የተሰወረ አይደለም።
“የኢጣሊያ ቅኝ ገዥዎችም የኤርትራ ተወላጆች ኢትዮጵያዊ ማንነትና ኩራት ካልደበዘዘ በስተቀር ተረጋግተው መግዛት እንደማይቻላቸው ከወዲሁ በመረዳታቸው በሰሜን እና በደቡብ የሚገኙትን ትግርኛ ተናጋሪዎች /ትግራዮች/ እንዲከፋፈሉ ማሴር ጀመሩ። በዚህም መሰረት በሁለቱም በቋንቋ፣ በባህልና በሃይማኖት አንድ የሆኑ ህዝቦች መካከል የመናናቅ፣ የጥላቻና የቁርሾ መርዝ በመርጨት ለዘመናት የሚዘልቅ ቅራኔ እንዲፈጠር አደረጉ” (ገፅ 34)።
መረጃ በማሰባሰብ ወቅት ደራሲው ከጣልያን ያገኛቸው ሰነዶች ያሰራጩ የነበሩት ቅስቀሳ ከገመተው በላይ እንደሆኑበት ይገልፃል። በዚህ ቅስቀሳ “ከመረብ ወንዝ በሰሜን የሚኖሩት ትግራዮች በደቡብ ከሚኖሩት ይበልጥ ስልጡኖች፣ ጥበበኞች እና አዋቂዎች እንደሆኑ የሚሰብኩ ከእውነታ የራቁ የኢጣሊያ መርዛማ የኘሮፖጋንዳ ስርጭቶች ምን ያህል የሕብረተሰቡን አመለካከት እንዳዛቡት መረዳት ችያለሁ” (ገፅ 34)። ከዚህም አልፈው ጣልያኖች የኤርትራ ተወላጆች ከትግራይ ጋብቻ እንዳይፈፅሙ የሚያግድ አዋጅ በእ.ኤ.አ በ1928 ዓ.ም እንዳፀደቁ ደራሲው ገልጿል (ገፅ 35ን ይመልከቱ)።
ጣልያኖች ያደረጉት “የኤርትራ ተወላጆች ልዩ ናችሁ” ስብከት አላማ፣ ደራሲው በሁለት ነጥብ እንደሚከተለው አጠቃሎታል፤
“1ኛ. የሰሜን ትግራዮች የሆኑት የኤርትራ ተወላጆች ኢትዮጵያዊ ማንነታቸውን ክደው በተለይም ወንድሞቻቸው ከሆኑት የደቡብ ትግራዮች የተለዩ መሆናቸውን አምነው ግንኙነታቸውን በማቋረጥ በኢጣሊያ ቅኝ ግዛት ሥር እንዲኖሩ እና ተገዥነታቸውን እንዲቀበሉ ማድረግ፤ (ገፅ35)
“2ኛ. ፋሺስት ኢጣሊያ የተቀረውን የኢትዮጵያ ግዛት በመውረር በቅኝ ግዛቱ ሥር ለማድረግ በሚያካሂደው ወታደራዊ ወረራ የኤርትራ ተወላጆች የሆኑ ትግራዮች ተባባሪ እንዲሆኑ እና በወረራው እንዲሳተፉ ማድረግ ናቸው” (ገፅ 36)።
ጣልያኖች የመጀመሪያው አላማቸው በተወሰነ ደረጃ የተሳካ ቢሆንም፣ ሁለተኛው አላማቸው ግን ሙሉ በሙሉ ማለት በሚቻልበት ሁኔታ ከሽፏል። በታሪክ እንደሚታወቀው ጣልያን የአድዋ ላይ ሽንፈቷን ቁጭት ለመበቀል ባደረገችው ዳግም ጦርንት አሰልፋቸው ከነበሩት መካከል በርካታ የኤርትራ ተወላጆች እየኮበለሉ ከኢትዮጵያውያኖች ጦር ጋር ተሰልፈው ታግለዋል። በእዚህ ላይ በወቅቱ ስለተደረገው የአርበኝነት ተጋድሎ የተፃፉ መፅሀፎችን መመልከቱ ይጠቅማል። ለምሳሌ፣ ኮሎኔል በላይ ኃይሌአብም ጥቁር አንበሳን በ1928 ዓም በመመስረትና በመምራት የአርበኘነት ተጋድሎ ያደርጉ የኤርትራ ተወላጅ ናቸው።
ቀጥተኛ መረጃ በመሰብሰብ ስለጎንደር አርበኞች የትግል ታሪክ በሚያስደንቅ ዝርዝር በፅሁፍ ያሰፈሩልን ገሪማ ታፈረም (1949፡55) “በውጋዴና እንዲሁም በሌላው አገር የጦር ግንባር በኩል ብዙ ኤርትራውያን ከጠላት የጦር ሠራዊት እየወጡ ከኢትዮጵያ የጦር ሠራዊት ጋራ በመቀላቀል በዋናውም ጦርነት ይልቁንም በአርበኝነት ለውድ እናት አገራቸው መሥዋዕት በመሆን በየጋራውና በየሸንተረሩ ደማቸውን ያፈሰሱት እጅግ ከቁጥር የበዙ ናቸው” በማለት በዝርዝር ኤርትራውያን ያደረጓቸውን ተጋድሎዎች አቅርበውልናል (ከገፅ 55 ጀምሮ ያሉትን ቀጣይ ገፆች ይመልከቱ)።
ለተጨማሪ ከብዙ በጥቂቱ በቅርቡ ወደአማርኛ የተመለሰውን የሀበሻ ጀብዱን፣ እንዲሁም የታደሰ ሜጫ ጥቁር አንበሳን ብቻ መመልከቱ በቂ ይመስለናል። ደራሲውም በዚህ ላይ በተለያዩ የሀገሪቷ ክፍሎች በተደረጉት ግንባሮች ኤርትራውያን ከኢትዮጵያውያን ሀይሎች ጋር የተሳተፉበትን ተጋድሎ እና መስዋእትነት በዝርዝር አቅርቧል።
4. በኤርትራ የትጥቅ ትግል አመሰራረትና እድገት
ጣልያን ኢትዮጵያን ዳግም ስትወር የኤርትራ ተወላጆችን አሳምና ህዝባቸውን እንዲወጉ ያደረገችው ጥረት እንዳሰበችው ባይሳካላትም፣ “ልዩ ናችሁ” የሚለው ትርክቷ በተወሰነው የማህበረሰብ ክፍል ዘንድ መስረፅ ችሎ ነበር። ይኸው ትርክት የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ሴራ ተደርቦበት በኤርትራ ወደሰላሳ ዓመት ለዘለቀው ጦርነት የፖለቲካ ግንባሮች መሰረት መሆኑ አልቀረም። ለዚህ ማሳያ በሻእቢያ ሬድዮ በወቅቱ ይነዙ የነበሩትን የኢትዮጵያ ህዝብን የሚያንቋሽሹ ቅስቀሳዎች ብቻ መገምገሙ በቂ ይመስላል።
ደራሲው ኤርትራ በእንግሊዝ ሞግዚት አስተዳደር ስር በነበረችበት ወቅት ስለነበረው ሁኔታ፣ የፖለቲካ እና የሲቪክ ማሕበራት፣ ኤርትራን ከኢትዮጵያ በፌደሬሽን ለማዋሀድ ስለተደረገው ጥረት፣ ፌደሬሽኑን በማፍረስ እራሳቸው የኤርትራ ተወላጆች እንጂ አሁን ኢትዮጵያ ጠል ፖለቲከኞች እንደሚተርኩት አለመሆኑን በስፋት አትቷል። ይህ በእርግጥ ለአብዛኛው የኢትዮጵያም ሆነ የኤርትራ ሰው የተደበቀ አልነበረም (አማኑኤል ገብረየሱስ፣ ግል ግንኙነት)። በወቅቱ በፕሮፕጋንዳ የሚነዙትን ደራሲው በሚከተለው መልክ ሞግቷል፤
“በ1960ዎቹ እና በ1970ዎቹ የነበሩት ፀሐፊዎችና አብዮተኞች ኤርትራ በኢጣሊያ የባእድ አገዛዝ ሥር በነበረችበት ወቅት አዲስ ኤርትራዊ ማንነት መፈጠሩን ገልፀዋል። ይህ ድምዳሜ ግን ከተጨባጭ እውነታ ጋር የሚቃረን መሆኑ ሁሉም ይገነዘበዋል። የኤርትራ ተወላጆች አንድ አገራዊ ኤርትራዊ ማንነት መፍጠር ይቅር እና የአካባቢው ጎሳዎች እርስ በእርስም በቅጡ የሚተዋወቁ አልነበሩም። ገና የእንግሊዝ አገዛዝ እንደተጀመረ እ.ኤ.አ በ1941 ዓ.ም የአስመራ ነዋሪዎች 40,000 የሚገመት ሰልፈኛ አስተባብረው የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ እያውለበለቡ የእንግሊዝን አስተዳደር በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ አካሄዱ። በሁኔታው የተደናገጠው የእንግሊዝ አገዛዝ ተወካይ ኬኔዲ ኩክ የሰልፉን አስተባባሪዎችን እንዲታሰሩ ከአደረገ በኋላ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ማውለብለብ ወንጀል መሆኑን የሚደነግግ ሕግ እንዲታወጅ አደረገ” (ገፅ 52)።
የሀገር ፍቅር ማሕበር ምስረታም ከዚህ ሰላማዊ ሰልፍ በኋላ እንደሆነ ደራሲው ይገልፃል (ገፅ 53ን ይመልከቱ)። በወቅቱ “እንግሊዛዊው የኤርትራ አስተዳዳሪ ብርጋዲየር ሎንግሪግ እ.ኤ.አ በ1944 ዓ.ም ወደ ለንደን ባስተላለፈው መልዕክት ‘ትምህርት የቀሰመው ሁሉም ኤርትራዊ ወጣት የአንድነት ታጋይ ነው’ በማለት ገልጿል” (ገፅ 60)። በዚሁ ኤርትራ በእንግሊዝ አስተዳደር ስር በነበረችበት ወቅት የተለያዩ የሲቪክ እና የፖለቲካ ማሕበራት ተቋቁመው ነበር። ከእነዚህ ውስጥ በጣም የሚታወቀው ከላይ የጠቀስንው የአንድነት ማሕበር የሚባለው ነው። ይህ ማሕበር ኤርትራን ወደኢትዮጵያ ለመቀላቀል በማለም ከተለያዩ ተቃዋሚዎች ጋር ቀላል የማይባል ተጋድሎ አድርጓል። ስለዚህ ማሕበርና ስለአደረገው ተጋድሎ ደራሲው የሚከተለውን ይላል፤
“የአንድነት ማሕበር ከኢትዮጵያ ጋር መዋሃድን ምርጫቸው ያደረጉ ትግርኛ ተናጋሪዎች /የሰሜን ትግራዮች/፣ በእምነትም የኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስትያን ሃይማኖት ተከታዮች በአባልነት የታቀፉበት ድርጅት ነው። ከዚህ በተለየ ሁኔታ በከንቲባ ዑስማን ህዳድ የሚመሩ የሐባብ እና ሳሕል ተወላጆች፣ የሚኒፍረ ባላባት ዓሊበይ፣ የዓሳውርታ ባላባት ናስር ፓሻ፣ አብዛኞቹ የሰምሃር /ምፅዋ አካባቢ/ ባለፀጋዎች ያሉበት የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ የሆኑ ሕዝቦች የአንድነት ማሕበር አባላት ከኢትዮጵያ ጋር ሕብረትን የሚደግፉ ናቸው። የእንግሊዝና የኢጣሊያ ቅኝ ገዥዎች መሳሪያ የሆኑት ራቢጣ አልኢስላሚያ፣ ሊበራል ኘሮግሬሲቭ ፓርቲና ሻራ ኢጣሊያ ግንባር ፈጥረው በአንድነት ማሕበር አባላት ላይ የተቀነባበረ ሴራ እና ጥቃት ቢፈጽሙም የአንድነት ኃይሎች ሴራውን በብቃት በመመከትና በማክሸፍ የበላይነታቸውን ማረጋገጥ ችለዋል። በመጨረሻም የተነሱበትን የአንድነትና የሕብረት ዓላማን አሳክተዋል” (ገፅ 65)።
በኤርትራው የጦርነት የትግል ታሪክ ከመነሻው ትልቅ ድርሻ የነበረው የኤርትራ ነፃነት ግንባር ወይም ጀብሀ በመባል የሚታወቀው ነው። ይህ ግንባር ደራሲውም እንደገለፀው “ሀይማኖታዊና አረባዊ ተልእኮን በማንገብ በግብፅ መንግስት አስተባባሪነት እ.ኤ.አ በ1960 ዓ.ም በካይሮ የተመሰረተ የፖሊቲካ ድርጅት ነው” (ገፅ 86)። በዚህ ጉዳይ ላይ የሚከተለውን ከአንዳርጋቸው ጥሩነህ ይመልከቱ፤
“In the course of the 1950s, Gamal Abdel Nasser waged a propaganda campaign through radio broadcasts in the languages of the Horn of Africa advocating, among other things, the independence of Eritrea. [… I]n 1958, he began to provide military training to disaffected Muslim Eritreans in Egypt at a camp near Alexandria. It was the Eritreans in Egypt such as these who created ELF in 1960 and launched their guerrilla activities in the territory in the following year” (2015፡27)።
የአረቡ አለም ይህን እኩይ ተልዕኮውን ያሳካ ዘንድ በቅድሚያ ያደረገው በትምህርት ሰበብ ስኮላርሺፕ/ነፃ እድል እየሰጠ በአካባቢው የሚገኙ ሙስሊሞችን መልምሎ መውሰድ ነበር። ይህ ሁኔታ አሁንም በመላ አፍሪካ ማለት ይቻላል አረቦች በእምነት ሽፋን የራሳቸውን ድብቅ የፖለቲካ/የሀይማኖት አጀንዳ ለመፈፀም የሚጠቀሙበት ስልት ነው። የጀብሀ መስራቾችም በዚህ የነፃ ትምህርት በሚል ሽፋን በካይሮ የተማሩ በአረባዊ የእስልምና ፖለቲካ ፍልስፍና የተጠመቁ ነበሩ (ገፅ 88)። ከገንዘብ፣ ቁሳቁስ እና ከፖለቲካዊ ድጋፍ በተጨማሪ የአረብ ሀገሮች በተለይ ግብፅ፣ ኢራቅና ሶሪያ ወታደራዊ ስልጠናም በማድረግ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል።
አንዳርጋቸው ጥሩነህ (2015) በቅርቡ በታተመው መፅሀፋቸው እንደዘገቡት በ1960ዎቹ በሶሪያ ብቻ በወታደርነት የሰለጠኑት የጀብሀ አባላት በአጠቃላይ በሀረር ጦር አካዳሚ የሰለጠኑትን ያህል ነበሩ። ጀብሀ እየተጠናከረ ሲመጣ ስልጠናው በሶሪያና በግብፅ ምድር መደረጉ ቀርቶ በቀጥታ ጀብሀ በተቆጣረው መሬት ላይ መደረግ ተጀመረ። እዚህ እየገመገምን ያለንው መፅሀፍ ደራሲ በወቅቱ በኢራቆች የተሰጠውን ወታደራዊ ስልጠና በኤርትራ በረሀ የተካፈለ እንደሆነ ይገልፃል።
“የኢራቅ መንግስት ወታደራዊ ጠበብቶች ወደ ኤርትራ ተጉዘው ሳሕል /ዓራግ/ በተባለ ሥፍራ ኮማንዶዎችን አሰለጠኑ። የሶሪያ መንግስት በበኩሉ ከፍተኛ ወታደራዊ ባለሞያዎችን በመላክ የከባድ መሣሪያ አጠቃቀም፣ የመገናኛ ሬድዮ ኦፕሬተርነት እና የፈንጂ አሰራር እና አጠቃቀም ስልጠና እንዲካሄድ እገዛ አደረገ። እንዲሁም ወደ ሳሕል /ዓራግ/ የተላኩት የሶሪያ የሕክምና ባለሞያዎች የተለያዩ የሕክምና ትምህርቶችን ሰጡ። የዚህ መጽሐፍ አዘጋጅ በወቅቱ በኢራቃዊያን በተሰጠው የኮማንዶ ስልጠና ተካፍዬ የተመረቅኩ በመሆኔ የነበረውን ሁኔታ እና ፖለቲካዊ ዝንባሌ ከተጨባጭ እውነታ በመነሳት መተንተን እና መመስከር እችላለሁ (ገፅ 105)።”
በዚህ ስልጠና ወቅት መዝሙሩ ሁሉ ተለውጦ የዓረብ ማንነትን የሚያንፀባርቅ ሆኖ እንደነበር ደራሲው ይገልፃል። ኢራቃዊ አሰልጣኞቻቸውም ሰልጣኖቹ አረብኛ ባለመቻላቸው ይገረሙ ነበር (ገፅ 107)። የመገረማቸው ምክንያት ሰልጣኞቹ አረቦች እንደሆኑ ለኢራቃዊ አስልጣኞቹ ተነግሯቸው ስለነበር ነው (ዝኒከማሁ)። በስልጠና ወቅት ይዘምሩ የነበሩት መዝሙር ከእነአማርኛ ትርጉሙ የሚከተለው ነው፤
አና ኤ - አና ዓረቢ
ዓረቢ ኤ- ዓረብ በለዲ
/ ዓረብ ምንድን ነው - ዓረብ የእኔ አገር ነው
እኔ ማን ነኝ - እኔ ዓረብ ነኝ።/ (ገፅ 107)
በጀብሀ ውስጥ ስለነበረው የሀይማኖት ሽኩቻ እንዲሁም ነፃነት ወይም ለፍትህ የሚደረግ ትግል የሚለውን ብሂል አምነው በተቀላቀሉት በተለይ ክርስትያን ወጣቶች ላይ ይደርስ የነበረውን ግፍ በዝርዝር ደራሲው አትቷል። ለአብነት ከመፅሀፉ የተቀነጨበውን የሚከተለውን ይመልከቱ፤
“የጀብሃ አመራር ግን የክርስትና እምነት ተከታይ የሆኑ የኤርትራ ተወላጆችን በትግል አጋርነት ለመቀበል ዝግጁ ስላልነበረ ‘የኢትዮጵያ መንግስት ሰላዮች ናችሁ’ የሚል የሃሰት ውንጀላ እየለጠፈ የእስር እና የግድያ ሰለባ እንዲሆኑ አደረገ። ይህንን የጀብሃ አሰቃቂ የግፍ ተግባር የተመለከቱ ወጣት ኤርትራዊያን ከጀብሃ አምልጠው ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል። የማምለጥ ዕድል ያላገኙት እና በጀብሃ እስርቤት የተቆለፈባቸው ‘የአዲስ አበባ ሃይል’ /ብስረያ አዲስ/ የሚል ታርጋ የተለጠፈባቸው 250 ወጣት የኤርትራ ተወላጆች በጀብሃ ግዚያዊ ጠቅላይ አመራር /ቃይዳ አልዓማ አልሙውቃታ/ ውሳኔ በጥይት ተደብድበው ተገድለዋል። ከተረሸኑት ውስጥ ግንባር ቀደም ታጋዮች የነበሩ ኪዳነ ክፍሉና ወልደይ ግደይ የተባሉ ኤርትራዊያን ትግራዮች ይገኙበታል። እነዚህ ወጣቶች ትግርኛ ተናጋሪዎች /የሰሜን ትግራዮች/ ከመሆናቸው ሌላ ምንም ወንጀል አልነበረባቸውም። የጀብሃን እስራትና ግድያ አምልጠው ወደ ኢትዮጵያ ከገቡት ግንባር ቀደሞች ውስጥ ሙሴ ተስፋሚካኤል እና ሃይለ ወ/ ትንሳኤ /ሃይለ ድሩዕ/ ተጠቃሾች ናቸው” (ገፅ 93)።
ደራሲው በወታደራዊ ስለጠና ወቅት ያጋጠመው የጀብሀን ማንነትና አላማ የበለጠ እንዲጠይቅ አደረገው፤ “ወደ የኮማንዶ ስልጠና ከመግባቴ በፊት ጀብሃ የዓረባዊና እስላማዊ ተልዕኮ አስፈፃሚ መሆኑ ከአጠቃላይ ሁኔታ ይገባኝ የነበረ ቢሆንም ዓራግ እንደገባን ‘እኔ ዓረብ ነኝ’ እያልን መዘመር ስንጀምር ሁሉም ነገር ግልፅ ሆነልኝ። ዓራግ የጀብሃን ዓረባዊና እስላማዊ ገመናን የገለፀችልኝ ትምህርት ቤቴ ስለሆነች ምንግዜም አስታውሳታለሁ” (ገፅ 107)።
ጀብሀ በመጨረሻም በወያኔ ድጋፍ በሻእቢያ ተሸንፎ ከኤርትራ ትግል እንደተሰናበት ደራሲው ይገልፃል፤
“የሻዕቢያ እና የህወሓት ሰራዊት ጥምረት በአምባሶይራ ተራራ በመሸገው የጀብሃ ኃይል ላይ ጥቃት በመፈፀም እንዲደመሰስና የተረፈውም ወደ ሸመጃና፣ ሃዘሞ እና ሰራየ እንዲበታተን አስገደደው። የሁለቱም ድርጅቶች ወታደራዊ ግንባር የተበተነውን የጀብሃ ሰራዊት እግር እግር እየተከታተለ እረፍት ስለነሳው ወደ ምዕራብ ኤርትራ ጠረፍ ወደባርካ ተጠቃሎ ሸሸ። በመጨረሻ በባርካ ላይ በተከፈተው የማጠቃለያ ውጊያ የጀብሃ ሰራዊት ተሸንፎ ወደ ሱዳን ተበታተነ። ከተቀናጀው የሁለቱም ድርጅቶች የማጥቃት ዘመቻ በኋላ ጀብሃ ፈርሶና ተበታትኖ በታሪክ ብቻ የሚወሳ ድርጅት ሆኖ ቀረ” (ገፅ 114)።
ደራሲው የሻእቢያን ከአመሰራረት አንስቶ በውስጥ ስለነበረው ሽኩቻ በስፋት በአራት ክፍል ከፋፍሎ ዳሷል። ዝርዝሩን ለአንባቢ እንተዋለን። ስለሻእቢያው ሊቀመንበር፣ የአሁኑ የኤርትራው ፕሬዘደንት ደራሲው በጎ አመለካከት እንደሌለው ከአቀረባቸው ገለፃዎች መረዳት ይቻላል። ይሁን እንጂ ደራሲው ፕሬዘደንቱ እንደሌሎቹ የፈጠራ ታሪክ የሚያምኑ ሳይሆን፣ ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል እንደነበረችና በኢትዮጵያዊው ማንነታቸው ላይ አንዴም ሲከራከሩ እንዳልተሰማ ገልጿል።
የሚከተለውን ለአብነት ይመልከቱ፤ “ኢሳያስ አፈወርቂ ኢትዮጵያዊ ማንነቱን ክዶ አያውቅም፤ ‘እኔ አትዮጵያዊ አይደለሁም’ ብሎም አያውቅም። ከጥንታዊቱ ኤርትራ ጋር በተያያዘ እንደ ሃገርም እንደ ማንነትም ሌሎች እንደሚመኩት ኢሳያስ አፈወርቂ ሲመካ አልተሰማም። ስለ አሁኒቷ ኤርትራ ግን እሱ እራሱ የፈጠራት አገር እንደሆነች እና ካለ እሱም ትርጉም የሌላት አገር እንደሆነች ደጋግሞ ሲመካ ተሰምቷል። […] ኢሳያስ የማንነት ቀውስ የለበትም” (ገፅ 17)። በአንድ ወቅት ፕሬዘዳንቱ በፕሪንስተን ዩኒቨርሲቲ ሀዝባዊ ንግግር ባደረጉበት ወቅት ከታዳሚዎች “እናንተ ኢትዮጵያውያን አይደለንም ትላላችሁ፣ ለመሆኑ ለዚህ የታሪክ ማስረጃችሁ ምንድነው?” ብለው ለተጠየቁት መልስ ሲሰጡ ኤርትራውያን ኢትዮጵያዊ ከመሆናቸውም በላይ፣ ቀዳሚዎቹ ኢትዮጵያውያን እነሱ እንደሆኑና የተለያዩት በፖለቲካ ልዩነት ብቻ መሆኑን እንደገለፁ በወቅቱ በስብሰባው ላይ የነበሩት ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሀቅና የዘ ሪድ ሲ ፕረስ ባለቤት አቶ ካሳሁን ቸኮል አጫውተውኛል።
“ኢሳያስ አፈወርቂ ኢትዮጵያዊ ማንነቱን ክዶ አያውቅም፤ ‘እኔ አትዮጵያዊ አይደለሁም’ ብሎም አያውቅም። ከጥንታዊቱ ኤርትራ ጋር በተያያዘ እንደ ሃገርም እንደ ማንነትም ሌሎች እንደሚመኩት ኢሳያስ አፈወርቂ ሲመካ አልተሰማም። ... ኢሳያስ የማንነት ቀውስ የለበትም”
5. ማጠቃለያ
ደራሲው በቀዳሚ ክፍሎች ስለዳሰስናቸው ጉዳዮች ብቻ ሳይሆን፣ ኤርትራ እንደሀገር ከቆመች በኋላ ስላለው የህብረተሰቡ ህይወት/ፖለቲካ እና አስተዳደር አንስቷል። ዛሬ የኢትዮጵያንና የኤርትራን ጉዳይ አንስቶ ማውራቱ እጅግ ተቀዛቅዟል። ምክንያቱ ኤርትራ እራሷን የቻለች ሀገር በመሆኗ አይደለም። ከላይ እንደገለፅንው ለፖለቲካ ትግሉ መነሻ የኢኮኖሚ ጥያቄ ወይም አንዳንዶች እንደሚሉት የባህል ጥያቄ ሆኖ አይደለም። ፖለቲካው “ልዩ ነን” በሚል ከታሪክም ሆነ ከእውነት በራቀ ፍልስፍና ላይ የተመሰረተ ነበርና ሁለት ሀገሮች ከሆኑም በኋላ ችግሩ መፍትሄ አላገኘም። የማንነት ልዩነትን የፖለቲካ ሰበብ አድርጎ መታገል ማቆምያ የለውምና ኤርትራ በራሷ የውስጥ ችግር ስትተበተብ፣ ኢትዮጵያም ከኤርትራ “ፖለቲካ” ቡድኖች ከተማሩት በመነሳት ማንነትን መሰረት ባደረገ በልዩነት ፈረስ የሚጋልቡ ድርጅቶች እንደአሸን ፈሉባት።እነዚህ ቡድኖች በፈጠሩት ቀውስ ኢትዮጵያም ተተበተበች። ይህም ስለኤርትራና ኢትዮጵያ ጉዳይ የሰከነ የእውነት ፍለጋ መድረክ በአካዳሚውም ሆነ በፖለቲካው ዘንድ እንዳይደረግ መጋረጃ ሆነ።
በማነነት ላይ የተመሰረተ የጎጥ ፖለቲካ ክፋቱ ልዩነቱ የታሰበው ላይ አለመቆሙ ነው። ጠላቴ የሚለው ወገን ሲዳከም ወይም የጠፋ ሲመስለው ልዩነቱ ወደታች ወርዶ እስከቤተሰብ ሊደርስ ይችላል። ለዚህ አብነት የጎረቤታችን ሶማልያን ሁኔታ መጥቀሱ ብቻ በቂ ማሳያ ይመስለናል። ሱማሊያዊያን እንደሀገር አንድ ለመሆን የሚያግዳቸው የነገድም ሆነ የቋንቋ ልዩነት ባይኖራቸውም፣ የልዩነት ፖለቲካ ወርዶ ጎጥ ላይ በማረፉ ሰላም ያለው አንድ ሀገር መፍጠር ተስኗቸዋል።
ልዩነት እንፈልግ ካልን የሌለበትን ማግኘት ነው የሚከብደው። እጅግ በሚመሳሰሉ መንታዎች መሀከል መለያ የሚሆን ነገር አይጠፋም። ቀኝ እጅና ግራ እጅ ጥንካሬያቸው እኩል አይደለም። ቀኝ ዓይንና ግራ ዓይን የማየት ችሎታቸው በተለይ በእድሜ ሲገፋ እኩል ላይሆን ይችላል። ኢትዮጵያና ኤርትራ ብቻ ሳይሆን ቢያንስ በባህል፣ በቋንቋ እና በነገድ የሚገናኙትን ሱማሊያን እና ጅቡቲን ጨምሮ (ከተቻለ በምስራቅ አፍሪቃ ወይም በአጠቃላይ አፍሪካ) የፖለቲካ ውህደት ማድረግ ቢያቅታቸው፣ የኢኮኖሚ ውህደት አድርገው ህዝባቸውን ከድህነት ማውጣት ላይ ቢያተኩሩ መልካም ነበር። ይህን ለማድረግ ህዝባቸውን ከማሳመን በላይ በመከፋፈላቸው እና በድህነታቸው የሚነግዱ የውጭ አትራፊዎችን በፖለቲካው ረገድ መዋጋት ይጠበቅባቸዋል።
እንደዜጋ እያንዳንዱ ምሁር ከግዚያዊ አጉል ውደሳ ርቆ እውነትን ከፈጠራ ታሪክ ለይቶ ለማሳየት የበኩሉን መወጣት ይጠበቅበታል። በእነዚህ ሀገሮች ያለው ችግር የተለያየ ባንዲራ የመትከል ጉዳይ አይደለም። ሁለት አይደለም አስርም ባንዲራ መያዝ ይቻላል። ችግሩ ባንዲራ በመትከልና እና የተለያየ ትንንሽ ሀገር በመፍጠር የሚፈታ አይደለም። እውነትን ተጋፍጦ ለህብረተሰቡ እድገት በጋራ የሚሰራበት አውድን ከመፍጠር ላይ ማተኮር ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ ደም የተከፈለበት ባርነት የፈጠራ ታሪክን ከስር ከመሰረቱ ለመናድ እና እውነትን ለማውጣት የተደረገ አስተማሪ ስራ ሆኖ ነው ያገኘሁት።
ዋቢ ፅሁፎች
ሌቪን = Levine, Donald N. 1974. Greater Ethiopia: The Evolution of a Multiethnic Society. Chicago: University of Chicago Press.
ታደሰ ሜጫ። 1933። ጥቁር አንበሳ። አስመራ፤ የኩሪዬሩ ኤርትሬኦ ማህበር ማተሚያ ቤት።
ትሪሚንግሀም = Trimingham, J. Spencer. 1952/1965. Islam in Ethiopia. London: Oxford University Press/Frank Cass & Co. Ltd.
አንዳርጋቸው = Andargachew Tiruneh. 2015. The Emergence and Proliferation of Political Organizations in Ethiopia. Los Angeles, CA: Tsehai Publishers.
አዶልፍ ፓርለሳክ (ተርጓሚ ተጫነ ጆብሬ መኮነን)። 1997። የሀበሻ ጀብዱ። አዲስ አበባ፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕረስ።
ኡለንዶርፍ = Ullendorff, Edward. 1960. The Ethiopians: An Introduction to Country and People. London: Oxford University Press.
ገሪማ ታፈረ። 1949። ጎንደሬ በጋሻው። አዲስ አበባ፤ ተስፋ ገብረ ሥላሴ ማተሚያ ቤት።
ግርማ አውግቸው ደመቀ። 2018 (እኤአ)። ቋንቋና ነገድ በኢትዮጵያ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ማንነትና ቅድመታሪክ፣ ቅፅ አንድ። ትሪንተን፤ ዘ ሬድ ሲ ፕረስ።