በጊዜያዊነት በመንግሥት ድጎማ ሳቢያ መጠነኛ የዋጋ ቅናሽ ላይ የነበረው የአውስትራሊያ የነዳጅ ዋጋ ዛሬ ረቡዕ እኩለ ለሊት ላይ የድጎማውን ማብቃት ተከትሎ ጭማሪ የሚያሳይ ይሆናል።
ከነገ ሴፕቴምበር 29 / መስከረም 18 አንስቶ የ25 ሳንቲም የዋጋ ጭማሪን ያስከትላል።
የሩስያና ዩክሬን ጦርነት ጋር ተያይዞ አሻቅቦ የነበረውን የነዳጅ ዋጋ ለመቋቋም ያስችል ዘንድ ያለፈው የሞሪሰን መንግሥት እስከ ዛሬ ረቡዕ መስከረም 18 የሚዘልቅና የሚያበቃ የስድስት ወራት ጊዜያዊ የነዳጅ ዋጋ ድጎማ እንዲካሔድ አድርጎ ነበር።
የኑሮ ውድነትን ለመቋቋም እንዲያግዝ የነዳጅ ድጎማው ይቀጥል የሚሉ ድምፆች ቢሰሙም አዲሱ የአልባኒዚ መንግሥት ድጎማው በተቆረጠለት ቀን መስከረም 18 እንዲያበቃ ወስኗል።
በሌላ በኩል ግና የዋጋ ጭማሪው በኒው ሳውዝ ዌይልስና የአውስትራሊያ ካፒታል ቴሪቶሪ ቢያንስ ለአንድ ሳምንት ያህል ያህል የዋጋ ጭማሪ እንደሚያሳይ ተመልክቷል።
የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ማሽቆልቆልም የነዳጅ የዋጋ ንረት በእጅጉ እንዲያሻቅብ እንደሚአያደርግም ተስፋ አሳድራል።