የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኅዳር 11 ባወጣው መግለጫ "የሽብር ቡድኑ ከ60 ዓመታት በፊት የኦሮሞም የሌሎች የኢትዮጵያ ብሔረሰቦችም ሁሉ ጥያቄዎች የነበሩና ተመልሰው ያደሩ ጥያቄዎችን አንስቷል።
በተለይም ከለውጥ በኋላ በሥራ ላይ የዋሉ ጉዳዮችን ከማነብነብ ውጭ የሚቆጠርና የሚቋጠር አጀንዳ" ማምጣት አልቻለም ሲል የክሽፈቱ አስባብ ነው ያለውን ገልጧል።
የኮሙኒኬሽን አገልግሎቱ አያይዞም ተደራዳሪ ቡድኑ "መንግሥት አዝሎ መንግሥት ያድርገኝ" ከሚል የዘለለ አጀንዳ ይዞ አልቀረበም ሲል ትችት የሰነዘረ ሲሆን፤ የሰላም ንግግሩ ለውጤት ይበቃ ዘንድ ጥረት ሲያደርጉ ለነበሩ አካላት ምስጋናውን አቅርቧል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደህንነት አማካሪ፣ በደቡብ አፍሪካ ከሕወሓት ጋር ተደራዳሪ የነበሩትና በዳሬሰላሙ ንግግርም መንግሥትን ወክለው ተገኝተው የነበሩት አምባሳደር ሬድዋን በበኩላቸው በንግግሩ መክሸፍ የተሰማቸውን ቅሬታ ገልጠዋል።
ለድርድሩ ስምረት ጥረት ላደረጉቱም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በሌላም በኩል ተደራዳሪው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር - የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት መግለጫ "የኢትዮጵያ መንግሥት ፍላጎት የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት አመራር ትብብር ላይ ብቻ እንጂ፤ አገሪቷን ገጥመዋት ላሉ ስር የሰደዱ የደህንነትና ፖለቲካዊ መሠረታዊ ችግሮች ላይ" እንዳልሆነ አመላክቷል።
የታጣቂዎቹ ተደራዳሪ አካላት ኦሮሚያ ውስጥ ሁነኛ የሆነ መንግሥታዊ አስተዳደር ድርሻንና ሁሉም የኦሮሞ ፓርቲዎች ዕውቅና እንዲያገኙ መጠየቁ ለንግግሩ ክሽፈት አንዱ አስባብ መሆኑ ተጠቅሷል።
በኢትዮጵያ መንግሥትና የኦነግ ነፃነት ሠራዊት ከዳሬሰላሙ ሁለተኛ ዙር ንግግር ቀደም ሲል በዛንዚባር የመጀመሪያ ዙር የሰላም ንግግር አድርገዋል።