"ለሚቀጥለው ምርጫ በሊብራል ፓርቲ መሪነት እንደምዘልቅ እተማመናለሁ፤ መልካም ዕድሎች ብቻ ሳይሆኑ፤ ኃላፊነቶችም አሉብን" የተቃዋሚ ቡድን መሪ ጆን ፐሱቶ

"አብሮ መሥራትና ዕልባት ማበጀት አዋኪ ቢሆንም እንኳ ከበሬታ በተመላበት መንገድ አብረን በመሥራት ልንከውነው እንችላለን። የግድ በጋራ መሥራት አለብን። አለያ ግና ባለፉት ጊዜያት አጋምዶን ያለው ኅብረተሰባዊ ድርና ማግ ይበጠሳል" የተቃዋሚ ቡድንና ሊብራል ፓርቲ ምክትል መሪ አቶ ዴቪድ ሳውዝዊክ

J P.jpg

John Pesutto, Victoria opposition and Liberal Party Leader. Credit: SBS Amharic

የተቃዋሚ ቡድንና ሊብራል ፓርቲ መሪው አቶ ጆን ፐሱቶና ገዲብ አመራሮች ረቡዕ ኖቬምበር 13 / ሕዳር 4 አመሻሽ በጠሩት ፕሬስ ኮንፈረንስ ላይ በመድብለባሕል፣ ንግድ፣ የአገልግሎት ተደራሽነት፣ አቅም መጣኝ የሆኑ የቤቶች ችግሮችን መቅረፍንና ለኑሮ ውድነት መላ ማበጀትን አስመልክተው ተናግረዋል።

አቶ ፐሱቶ በተለይም ፍልሰተኛ ማኅበረሰባትን በተመለከተ ሲናገሩ " የእኛ ተግባር አዲስ ወደ ሃገራችን የመጡ ፍልሰተኞች ችግሮችና ለረጅም ጊዜያት ቆይተውም የመንግሥት ድጋፍ ባጡቱ ላይ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን ብርቱ ድጋፍ ማድረግንም ያካተተ ነው" ብለዋል።

አክለውም፤ ፓርቲያቸው የፍልሰተኛ ማኅበረሰብ አባላት ሁሉን አካታች የሆነ መንግሥት እንደምን እንደሚገነባ፣ ለትውልድ ተዛማጅ የሆነ ዕዳ ቅነሳ፣ የባቡር መሥመር የመሳሰሉ የመሠረተ ልማት አውታር ዝርጋታዎች፣ በአውስትራሊያና ከመጡባቸው ሀገራት ጋር ተዛማጅ በሆኑ የንግድ ግንኙነቶች ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ የሚያበረታታና የሚሠራ መሆኑን ገልጠዋል።

እስከ መጪው 2026 ክፍለ ሀገራዊ ምርጫ በአመራር ላይ የመቆየት ዕድላቸውን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱም "ለሚቀጥለው ምርጫ በሊብራል ፓርቲ መሪነት እንደምዘልቅ እተማመናለሁ፤ መልካም ዕድሎች ብቻ ሳይሆኑ፤ ኃላፊነቶችም አሉብን" ብለዋል።

የሊብራል ፓርቲ ምክትል መሪ ዲቪድ ሳውዝዊክ በበኩላቸው አቶ ፐሱቶን አስመልክተው ሲናገሩ "ጆን ተፋላሚ ነው። የሚፋለውም ግና ከቅን ልቦና ጋር
ነው" ብለዋል።

የመድብለ ባሕል ማኅበረሰባትንም በተመለከተ ሰዎች ከየትም ይምጡ ከየት፣ በማንነታቸውና ምንነታቸው ከበሬታ ሊቸራቸው እንደሚገባ አሳስበዋል።
David Liberal Party Deputy.png
David Southwick, Victoria Deputy Liberal Party Leader. Credit: SBS Amharic
አያዘውም "በተለያዩ ማኅበረሰባት ውስጥ ችግሮች እንዳሉ እናውቃለን። ሆኖም እኒያን ችግሮች በመቆስቆስ ቪክቶሪያ ውስጥ ልዩነቶችን መፍጠር አያሻም። አብሮ ለመሥራትና ዕልባት ለማበጀት አዋኪ ቢሆንም እንኳ ከበሬታ በተመላበት መንገድ አብረን በመሥራት ልንከውነው እንችላለን። የግድ በጋራ መሥራት አለብን። አለበለዚያ ግና ባለፉት ጊዜያት አጋምዶን ያለው ኅብረተሰባዊ ድርና ማግ ይበጠሳል" ሲሉም ልብ አሰኝተዋል።

ተለምዷዊው በተለያዩ የማኅበረሰባት ኩንቶች ላይ መገኘት፣ ድጎማ መስጠትና "እናመሰግናለን" ተባብሎ መሰነባበት ጠቃሚም ቢሆን ዘላቂ ሊሆን እንደማይችልም አመላክተዋል።

ይልቁን መታሰብ ያለበት እንደምን ዘላቂ እንደምናደርገው፣ የትምህርትና ሥራ ዕድሎች፣ ይወደፊት ዕጣ ፈንታን ቪክቶሪያ ውስጥ እንደምን መፍጠር እንደሚቻል በማሰብ በጋራ መሥራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በፊናቸው ጤናን የመሳሰሉ አግለግሎች መዳከምን ያነሱ ሲሆን "እኛ የምርጫ፤ የመልካም ዕድል ፓርቲ ነን" ያሉት የተቃዋሚ ቡድኑ የላይኛው ምክር ቤት መሪ የሆኑት ጆርጂ ክሮዚየር የቀድሞ የነርስና አዋላጅ ሙያቸውን ሥነ ምግባር አጣቅሰው፤

"በሕክምና ዓለም አንድ ሰው ለሕክምና ሲመጣ ማንነው? ከየት ነው? ተብሎ አይጠየቅም፤ ከፍና ዝቅ ተደርጎ አይገመትም። የሚያሻው ክብካቤ ብቻ ነው፤ ያም ይደረጋል። የእዚያ ዓይነቱን አገልግሎት ነው ለመላው ቪክቶሪያውያን መስጠት የምንፈልገው" ብለዋል።

Gorgie Crozier.png
Georgie Crozier is a leader in the Legislative Council and shadow minister for health. Credit: SBS Amharic
በሌበር ፓርቲ በኩል የባቡር መሥመር ዝርጋታ የምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴ አንዱ አካል እንደሆነና የአገልግሎት ዘርፎችም ቅልጡፍ እንዲሆኑ ጥረቶችን እያደረገ መሆኑን ይገልጣል።


Share
Published 15 November 2024 8:29am
By Kassahun Seboqa Negewo
Source: SBS

Share this with family and friends