የቀድሞው የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ ታየ ደንደአ በተጠርጣሪነት ለእሥር የተዳረጉት በፌዴራል የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል ሲሆን፤ ግብረ ኃይሉ ታህሳስ 2 ቀን 2016 ባወጣው መግለጫ አቶ ታየ "ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከሚንቀሳቀሱ ፀረ ሰላም ኃይሎች ጋር በተሳሰር ለጥፋት ተልዕኮ በሕቡዕ ሲሰራ ተደርሶበታል" ብሏል።
መግለጫው አያይዞም " ተጠርጣሪዉ ታየ ደንደአ በህግ ቁጥጥር ሥር በዋለበት ወቅትም በመኖሪያ ቤቱ ዉስጥ በተደረገ ፍተሻ፤ ግለሰቡ በህቡዕ ለሚያደርገዉ ፀረ-ሰላም እንቅስቃሴ ሲገለገልባቸዉ የነበሩ የተለያዩ 9 ሞባይሎች፣ 4 ላፕቶፖች፣ 3 አይፖዶች፣ በርካታ ፍላሾች፣ 2 የፊትና የኋላ የተለያዩ ተሸከርካሪ ሰሌዳዎች እና ልዩ ልዩ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች፣ ክላሽንኮቭ ጠመንጃና ሽጉጦች ከመሰል ጥይቶች ጋር እንዲሁም የኦነግ ሸኔ አርማዎችና በተለያዩ ግለሰቦች ስም የተዘጋጁ የኦነግ ሸኔ መታወቂያዎች፣ ሰነዶችና ማስታወሻዎች ተገኝተዋል" ሲል አስታውቋል።
የፌዴራል ፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ የአቶ ታየ መኖሪያ ቤት ፍተሻ በተደረገበት ወቅት በሶስት መታወቂያዎች የሚጠቀም አንድ የኦነግ ሸኔ አባል ተደብቆ መገኘቱን የገለጠ ሲሆን፤ በመንግሥትና በፖርቲ መዋቅር ዉስጥ ሆነዉ በተመሳሳይ ድርጊት በተሰማሩ አካላት ላይም ግብረ ኃይሉ ክትትል በማድረግ ላይ እንደሆነና ውጤቱንም ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግ አክሎ ገልጧል።