የዩናይትድ ስቴትስ ምክትል ፕሬዚደንት ካማላ ሃሪስ በዋሽንግተን ዲሲ ሃዋርድ ዩኒቨርሲቲ ተገኝተው ለደጋፊዎቻቸው ባደረጉት ንግግር ዶናልድ ትራምፕ የ2024 ፕሬዚደንታዊ ምርጫ አሸናፊ መሆናቸውን አምነው መቀበላቸውን ገለጠዋል።
ዶናልድ ትራምፕ የ72 ሚሊየን አሜሪካውያንን ድጋፍና 295 የምርጫ ኮሌጅ ድምፅ ሲያገኙ፤ ካማላ ሃሪስ የ67 ሚሊየን መራጮችን ድጋፍና 226 የምርጫ ኮሌጅ ድምፅ ማግኘታቸውን የ90 ፐርሰንት የምርጫ ቆጠራ ውጤት አሳይቷል።
ምክትል ፕሬዚደንት ሃሪስ በንግግራቸው ወቅት "ውጤቱን መቀበል አለብን። ከተመራጭ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ተነጋግሬያለሁ፤ ድላቸውንም አስመልክቼ እንኳን ደስ ያለዎት ብያቸዋለሁ። እንዲሁም፤ ለሚያደርጉት ሽግግር እሳቸውንና ቡድናቸውን እንደምናግዝና ለሰላማዊ የስልጣን ሽግግሩም ተሳትፎ እንደምናደርግ ነግሬያቸዋለሁ" ብለዋል።
ደጋፊዎቻቸው ተስፋ ሳይቆርጡ ለመጪው ጊዜ ፍልሚያ ከማድረግ ወደ ኋላ እንዳይሉ አበረታተዋል።
ከሃሪስ ቀደም ብሎም የወቅቱ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ስልክ መትተው ዶናልድ ትራምፕን "እንኳን ደስ ያለዎት" ብለው አነጋግረዋል።
ተመራጭ ፕሬዚደንት ትራምፕም ድላቸውን አስመልከተው ለደጋፊዎቻቸው ባደረጉት ንግግር አሜሪካ እንድትፈወስና ድንበርን ጨምሮ ችግሮቿ ሁሉ በእሳቸው አመራር እንደሚፈታ ተስፋ ቸረዋል።
የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዚና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፔኒ ዎን ለዶናልድ ትራምፕ የእንኳን ደስ ያለዎት መልዕክት ልከዋል፤ ከትራምፕ አስተዳደር ጋርም አብረው ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጠዋል።