የኢትዮጵያ ዘውድ ምክር ቤት የካቲት 20 ባወጣው መግለጫ "የኢትዮጵያ ዘውድና ህዝቦች፤ በገዛ ወገኖቻችን የሚፈጸመውን፤ የወገኖቻችንን እልቂት ስንገነዘብና ስናዝን ለ50 አመታት ያህል ቆይተናል፡፡ ከአሁን በኋላ ግን ይህን የመሰለ ስቃይና ግፍ ማየትና መስማት አንችልም" ሲል "ለ50 ዓመታት የቀጠለው ዕልቂት ይቁም" በሚል መግለጫው አሳስቧል።
መግለጫው አያይዞም "በቅርቡ በጎጃም ጠቅላይ ግዛት በመራዊ ከተማ፤ ህጻናትንና አዛውንትን ጨምሮ፤ በኢትዮጵያ መለዮ ለባሾች ጥር 20 ቀን 2016 ዓ.ም የተፈጸመውን የ102 ንጹሃን ጭፍጨፋ ተገንዝበናል፡፡ ይህ ሆን ተብሎ የተፈጸመ አረመኔያዊ ጭፍጨፋና ግፍ ነው፡፡ ስለሆነም እንደዚህ ያለውን ድርጊት የምንችልበት ልብ ከአሁን በኋላ አይኖረንም፡፡ በመራዊ የተገደሉት ሰዎች ወንጀል፤ አማራነታቸው፤ የክርስቲያንና የእስላም ሃይማኖቶች ተከታዮች መሆናቸው ብቻ ነው፡፡ ገዳዮቹ ደግሞ ሆን ተብሎ በብዛት ከሌላ ብሄረሰብ ተወላጅ የሆኑ ወታደሮች ናቸው" ብሏል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት ብቻ፤ ወደ 1 ሚሊዮን የሚሆኑ ኢትዮጵያውያኖች እንደተገደሉ ግምት መኖሩን ያመላከተው የዘውድ ምክር ቤት መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም፤ የወታደራዊውን መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ ግርማዊ ቀዳሚዊ ኃይለሥላሴ አክሎ በ60 ከፍተኛ ባለስልጣናትና ቀይ ሽብርን ጨምሮ በሌሎችም ላይ የደረሰውን ግድያ አጣቅሷል።
"ባለፉት 50 አመታት፤ አብዮተኞች የከፋፍሎ መግዛት መርህ ይዘው፤ ኢትዮጵያዊነታችንን ለመቀማትና ለማጥፋት ሲጥሩ ቆይተዋል፡፡ በተጨማሪም፤ በእነዚህ አመታት ውስጥ፤ መሬታችንን፤ ንብረታችንን፤ በህግ ፊት ያለንን መብትና ተስፋችንን ተቀምተናል፡፡" ያለው መግለጫ "ከአሁን በኋላ ግን፤ የእኛ ያልሆነ ማንንት ሊሰጡን የሚጥሩትን አንቀበልም፡፡ እኛ፤ የአምላክ ቡራኬ ያለን፤ ነጻ ህዝብ የሆንና በክልል አጥር መለያየት የማንፈልግ ኢትዮጵያውያን ነን፡" ሲልም አክሏል።
በአሁኑ ወቅት፤ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍለግዛቶች የፍትሕ ትግል እንደተቀጣጠለ በማመላከትም "ሆኖም ግን፤ ፍትህና ተቀባይነት ያለው የህግ አስተዳር ካልመሰረትን፤ የምናደርገው ትግል ሁሉ ዋጋቢስ ይሆናል፡፡ ትግላችን ፍትህን ለማምጣት እንጅ፤ አንድን ግጭት በሌላ ግጭት የመቀየር አላማ መሆን የለበትም" ሲል አሳስቧል።
አያይዞም "በተለያዩ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ግዛቶችና ክፍለግዛቶች ውስጥ የተነሱትን የፋኖን ታጣቂ ቡድኖች የምናሳስበው፤ አላማቸው ፍትህንና ተጠያቂነትን ለማስከበርና በህዝቦቻችን መካከል ፍቅርና ብልጽግና እንዲመጣ ማድረግ እንጂ የበቀል ትግል መሆን እንደሌለበት ነው" በማለት የአሸማጋይነት ሚና አቅጣጫውን ሂደት አመላክቷል።
የዘውድ ምክር ቤቱ "ይህን የ50 አመታት እንባ፤ የተቃጠለ ጊዜና የእልቂት ዘመን፤ ወደፊትም የሚቀጥል ሳይሆን ያለፈ ትዝታ እናድርገው፡፡ በታላቆች ንጉሰነገስቶቻችን፤ በግርማዊ ዳግማዊ ምኒልክና በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ከተጀመሩት የኢኮኖሚና የማህበራዊ አውደ ሂደቶች መማርና እነሱም ማጠናከር ይኖርብናል፡፡ታሪክ በሚረሳቸው አምባገነን መሪዎች ወደኋላ የቀረችውን ኢትዮጵያን እንደ አዲስ እንገነባለን፡፡
"የአሁኑ አላማችን፤ በወቅቱ የሚካሄድውን ጦርነትና ግጭት፤ ብዙ የደም መፋሰስ ሳያስከትል አስቁመንና ቂም በቀልነትን አስወግደን፤ ሁሉን አቀፍ ፍትህ እንዲመጣ መጣር ነው" ብሏል።