በኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ከአውራዎች አንዱና ተወዳጁ ድምፃዊ አለማየሁ እሸቴ ዛሬ ነሐሴ 27/2013 ዓም እኩለ ሌሊት በድንገት ማረፉ ተገልጿል። የሙዚቃ ወዳጁ ቢላል መስፍንና የቤተሰቡ ቅርብ ወዳጅ ብርሃኔ ስዩም እንዳረጋገጡልኝ ተወዳጁ ድምፃዊ ዛሬ ሌሊት አርፏል።
የዛሬ ስድስት ወር ገደማ ከወዳጁና የቅርብ ጓደኛው አንጋፋው ሙዚቀኛ ግርማ በየነ ጋር ባደረኩት ቃለ መጠይቅ ወቅት ባገኘሁት መረጃ አለማየሁ እሸቴ በኢትዮጵያ የግል ሸክላ ሙዚቃ ህትመት ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያ የሆነበትን ሙዚቃ በአምሃ ሬከርድስ አማካኝነት ያሳተመ የዘመናዊ ሙዚቃ ባለሙያ ነበር አለማየሁ እሸቴ።
ለመጀመርያ ጊዜ በ1955 ዓ, ም በፖሊስ ሠራዊት ኦርኬስትራ በመቀጠር የሙዚቃ ሀሁን የጀመረው አንጋፋዉ ሙዚቀኛ አለማየሁ እሸቴ በወቅቱ በሚጫወታቸው የሙዚቃ ስራዎቹ ኤልቪስ ፕሪስሊ የሚል ቅፅል ተሰጥቶት ነበር። በተጨማሪም ከአማርኛ ዘፈኖች የጥላሁን ገሰሰን ሙዚቃዎች ያዜም እንደነበር እኤአ በ2015 በጀርመን ሀገር የሙዚቃ ሽልማት ባገኘ ወቅት ለጀርመን ድምፅ ተናግሮ ነበር።
ተማር ልጄ በሚለው አይረሴ መልዕክት አዘል ዘፈኑ የተነሳ እውቅና በተሰጠው በዚያ ወቅት እንደተናገረው "የዘፈኑን ዕድሜ ስነግራችሁ ሸመገለ እንዳትሉኝ እንጂ « ተማር ልጄ» የተዘፈነዉ የዛሬ ሰላሳ አምስት ዓመት ነዉ። ያዘለዉ መልዕክት እዉነተኛ አባት ለልጁ የሚሰጠዉ ምክር ነዉ። የሰዉ ልጅ ካልተማረ ዋጋ የለዉም። ስለሆነም አባቶች የሚሰጡንን ምክር በዚህ ዘፈን ለመጭዉ ትዉልድ የዘራሁት ነዉ ብዬ ነዉ የማምነዉ» ብሎ ነበር አለማየሁ እሸቴ።
አንጋፋው ድምፃዊ የኢትዮጵያን ዘመናዊ ሙዚቃ ከፍ ወዳለ ደረጃ ካደረሱት ድምፃዊያን መሃል አንዱ ለመሆኑ ግርማ በየነ እና ሙላቱ አስታጥቄ ቋሚ ምስክሮች ናቸው።
"ስቀሽ አታስቂኝ" ፣ " እንደ አሞራ ክንፍ አውጥቼ ልብረራ"፣ " ማን ይሆን ትልቅ ሰው" ፣ " ምሽቱ ደመቀ"፣ "አዲስ አበባ ቤቴ" ፣ "የወይን ሃረጊቱ" ፣ "የሰው ቤት የሰው ነው"፣ "ደንየው ደነባ"፤ "ትማርኪያለሽ"፣ "ወልደሽ ተኪ እናቴ" እና ሗሇ" ተማር ልጄ" ከአለማየሁ እሸቴ ሙዚቃዎች ዋነኞቹ ሆነው የሚጠቀሱለት ናቸው።
በአንጋፋ አርቲስቶች መዝገበ ሕይወት የሰፈረው ታሪኩ እንደሚያትተው አለማየሁ እሸቴ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በአርበኞች ት/ቤት እየተከታተለ ባለበት ወቅት ባደረበት ጥልቅ የሙዚቃ ፍቅር ነበር ፖሊስ ኦርኬስትራን የተቀላቀለው።
[ ደመቀ ከበደ ፡ አዲስ አበባ ]