"ጠ" እና "ፀ"

*** (ግጥም ፡ በደመቀ ከበደ)

Journalist Demeke Kebede

Journalist Demeke Kebede Source: Supplied

ታገሬ ወጥቼ - ከተማ ገብቼ

ገድ ቀናኝና - ካንቺ ተዋድጄ

አልችል ብል ልለምደው - የከተማን ኑሮ

በአነጋገሬ ላይ - አሰማሽ እሮሮ፤

‹‹ፀሐይ›› አልኩ ብዬ - ‹‹ጠሀይ›› በማለቴ

‹‹ፀጉር›› ልል ፈልጌ - ‹‹ጠጉር›› የሚልን ቃል - ከአፌ በማውጣቴ ተበሳጨሽና - ቁጣ አዘነብሽብኝ በ‹‹አድርግ››ና ‹‹አታድርግ›› - ግማሽ ቀን ዋልሽብኝ፤

 

‹‹ ‹ፀ› ማለት ሲገባህ - ‹ጠ›ን አትጥራ ሁሌ - ዳግም እንዳልሰማ እንዳታዋርደኝ እንዳታስፎግረኝ - በመሃል ፒያሳ - በነቃ ከተማ በቃህ አቁም በቃ - ዘወትር ‹ጠ› አትበል ‹ጠሎት›ንም ‹ፀሎት› - ‹ጠሀይ›ን ‹ፀሐይ› በል!››

 

ትዕዛዝሽን ላከብር - ምን ብጠነቀቅም

‹‹ጠ››ን በ‹‹ፀ›› ተክቼ - ተናግሬ አላውቅም፤

 

ይህን አየሽና…

 

‹‹ይቅር እንለያይ - በአንተ አልፈር እኔ

ከብጤህ ተዛመድ - አቻ ሽቷል ጎኔ!››

ብለሽ ተለየሽኝ - ያላንዳች ይሉኝታ

ባላወቅሁት ‹‹ቅጥበት›› - ባልገመትኩት አፍታ፤

ሳስበው አመመኝ…

ሰበብሽ ያበግናል - ያጨሳል፣ ያደብናል

ሰው እንዴት በቋንቋ - ፍቅርን ይመዝናል?

 

ታዲያ ምኔ ዋዛ - ምኔ ሞኝ ነውና

እኔም በተራዬ - እንተከተክ ጀመር - ‹‹ፀ››ን ተካሁኝና

ይኸው ይኸውና …

‹ፅፍራም› ነሽ፣ ‹ገፃፃ› - ፍቅር የማይገባሽ

‹ፀብ› እንጅ መዋደድ - ‹ፄና› የሚነሳሽ

እስኪ አሁን በሞቴ

ምኑ ነው ‹ፅፋቴ›?

በ‹ፀራራ› ፀሐይ - ‹ወክ› እናድርግ ማለቴ?

‹ፀርሙስ› ሙሉ ቢራ - በቀን ‹መፀፃቴ›?

በ‹ፀፀር› ጎዳና - ‹ፀጅ› ይዤ ‹መውፃቴ›?

ነው ወይስ ኮብልዬ - ከ‹ገፀር› ‹መምፃቴ›?

 

በያ ንገሪኛ

ምኑ ነው እሚያሳፍር - ይህ የኔ አማርኛ?

እኔ ግን ልንገርሽ?

በ‹ፀበልም› ባልድን - ባይለቀኝም ፍቅርሽ

አብሮ መውፃት መግባት - ሰርክ ካሳፈረሽ

ወይ ካሸማቀቀሽ

ከእኔ ጋር መታየት - ከሰው ካሳነሰሽ

ያውልሸ ጎዳናው - ሂጅ ወደፈለገሽ

‹ቢፄ›የን አላፃም

እኔ የሞፃው ልጅ

‹ፀብራራ›ው ‹ገፀሬ› - ‹ፃፃ› አለኝ መሰለሽ!!


Share
Published 19 December 2020 11:58am
By Demeke Kebede

Share this with family and friends